በእምነትና በብሄር ሊከፋፍሉን የሚሞክሩ የጥፋት ቡድኖችን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል- ጉባኤው - ኢዜአ አማርኛ
በእምነትና በብሄር ሊከፋፍሉን የሚሞክሩ የጥፋት ቡድኖችን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል- ጉባኤው
ጎንደር ፤ ግንቦት 2/2014(ኢዜአ) ''ኢትዮጵያውያን የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጠናከር በእምነትና በብሄር ሊከፋፍሉን የሚሞክሩ የጥፋት ቡድኖችን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል'' ሲሉ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ተናገሩ።
በጎንደር ከተማ የተፈጠውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና የህብረተሰቡን አብሮነት ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ የሀይማኖት አባቶች የምክክር መድረክ በከተማው እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያውያን ከመላው ዓለም የሚለየን በጠንካራ አብሮነትና መቻቻል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለዘመናት የዘለቀውን አብሮነታችንን ለመሸርሸር ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሁለቱን እምነት ተከታዮች ለመለያየትና ለማጋጨት የሚጥሩ ቡድኖችን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል ብለዋል።
በቤተ እምነቶች መካከል ተቻችሎ አብሮ መኖር ለኢትዮጵያውያን አዲስ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ሁሉም ቤተእምነቶች የሚመሰክሩት ታሪካዊ ሃቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የተጎዱ ወገኖችን መደገፍና ማፅናናት ብሎም በግጭቱ የፈረሱ ተቋማትን ዳግም በህብረት መገንባት እንደሚገባ አመልክተው፤ በእምነት ሽፋን ወንጀል የፈፀሙ ቡድኖችን ለህግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን ብለዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሃጅ ኡመር ኢድሪስ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍና የኢትዮጵያ ወንጌላዊ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዱን ጨምሮ 13 የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።