የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ6 ነጥብ 6 በመቶ የሚያድግ መሆኑን ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም አመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ6 ነጥብ 6 በመቶ የሚያድግ መሆኑን ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም አመላከተ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ6 ነጥብ 6 በመቶ የሚያድግ መሆኑን ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ማመላከቱን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ተናገሩ ።
የ2014 በጀት አመት ማክሮ ኢኮኖሚ የ6 ነጥብ 6 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብም ማሳያ ነው ብለዋል።
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ አለም አቀፋዊ ጫናዎችና የአገር ዉስጥ ጉዳዮች ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና እንደነበሩም ነው የጠቆሙት።
የኢትዮጵያ የ9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተገምግሟል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖም በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው ባላፉት 9 ወራት በተለይ በግብርና፣ ወጪ ንግድና አገልግሎት ዘርፎች ላይ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።በግብርና መስክ 336 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቅሰው፣ ከዚህም ውስጥ በበጋ መስኖ ልማት 25 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል ነው ያሉት፡፡
ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከወጪ ንግድ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ጠቁመው ከአገልግሎት ዘርፍም 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
በሌሎች ዘርፎች ላይም የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ ማደግ እንደሚችል ያመላክታል ነው ያሉት፡፡
ነገር ግን የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ በአገር ውስጥ የተከሰተው ድርቅ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ በማድረግ ማክሮ ኢኮኖሚውን በብርቱ መፈተኑን አብራርተዋል።
ለአብነትም ማዳበሪያ ከሁለት ዓመት በፊት በአንድ ቶን ከነበረበት የ250 ዶላር ዋጋ አሁን ላይ ወደ 1 ሺህ 300 ዶላር ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
የስንዴና የዘይት ዋጋ በጥርና መጋቢት ወራት ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 65 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን ገልጸው፤ ይህም በኢትዮጵያ ገበያ ላይ የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የዋጋ ግሽበትን ለመቋቋም የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዜጎች ሰላምና ጸጥታ በማስከበር ሂደት የድርሻቸውን በመወጣት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር አስተዋጥኦ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።