ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል

79

ግንቦት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ለሊሴ ነሜ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ 3 ነጥብ 63 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ዕቅድ ተይዞ ነበር።

ከዕቅዱም 2 ነጥብ 43 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን የተናገሩ ሲሆን የተመዘገበው ውጤት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ18 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል።

በእቅድ ወራቱ 203 ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ ታቅዶ 118 ባለለብቶች መሰማራታቸውን ገልፀዋል።

ከዚህም ውስጥ 65 በማኑፋክቸሪንግ 50 በአገልግሎትና ሦስት በግብርና ዘርፍ መሰማራታቸውን ጠቁመዋል።

ኢንቨስት ካደረጉ ባለህብቶች አብዛኛዎቹ ከቻይና የመጡ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በዘጠኝ ወራት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚላኩ ምርቶች 223 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 156 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል።

ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም የ27 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ ጥረቱ በርካታ ፈተናዎች እንደገጠሙት ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ከአጎአ ማዕቀፍ መሰረዝ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የሎጂስቲክስ ችግር፣ የሰላምና ጸጥታ ችግር እንዲሁም የዩክሬንና ሩሲያ ቀውስ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ከፈተኑት መካከል እንደሚገኙበት አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም