በኦሮሚያ ክልል ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት እየተሰራ ነው

54

አዳማ፣ ግንቦት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል በተያዘው የምርት ዘመን ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም በዋና ዋና ሰብሎች ለማልማት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልል ደረጃ የመካናይዜሽን እርሻ አገልግሎት በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ ዛሬ  በይፋ ተጀምሯል።

የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በ2014/15 የምርት ዘመን 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል በማልማት ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል።

ለዕቅዱ ስኬት የምርት ማሳደጊያ ግብዓት አቅርቦትና የእርሻ ማሳ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በክልሉ ደጋማና በስምጥ ሸሎቆ አካባቢ ያለውን ሰፊ መሬት በሙሉ በመካናይዜሽን ዘዴ ለማረስ ዛሬ በይፋ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

በክልሉ በምርት ዘመኑ የመኸር እርሻ ከሚለማው መሬት ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነው በመካናይዝድና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

አምና በኩታ ገጠም 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መታረሱን አስታውሰው፤ በዘንድሮ የምርት ዘመን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ፣ ከ180 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የገብስ፣ የበቆሎና ሌሎች የጥራጥሬ ሰብሎች ምርጥ ዘር በዩኒዬኖች በኩል ለአርሶ አደሩ እየደረሰ መሆኑን አቶ ጌቱ ጠቁመዋል።

ሊያጋጥም የሚችለውን የሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ለመፍታት ከወዲሁ በአርሶ አደሩ ከ42 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው አምና በኩታ ገጠም ከለማው ማሳ በሄክታር በአማካይ ከ40 ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ጠቅሰው፤ በኩታ ገጠም ልማቱ ያልተሳተፉ አርሶ አደሮች በሄክታር ያገኙት ትልቁ የምርት መጠን 18 ኩንታል መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ የእርሻ ማሳ ዝግጅት ቀድሞ የተጀመረው ሁሉም አርሶ አደሮች ዘንድ የመካናይዜሽን አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግና የተሻለ የግብዓት አቅርቦት እንዲያገኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ በበኩላቸው በኩታ ገጠም እርሻ ዋና ዋና ሰብሎችን ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኩታ ገጠም ተደራጅተው በመካናይዜሽ በማረሳቸውና የተሻለ ቴክኖሎጅ በመጠቀማቸው ውጤታማ መሆን መቻላቸውን አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

ከዘርና ማዳበሪያ አጠቃቀም ጀምሮ የተሻለ የመካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ለማግኘትና ውጤታማ ለመሆን የኩታ ገጠም እርሻ እጅጉን የተሻለ አማራጭ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም