የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች ተጎጂ ወገኖችን ለማፅናናት ጎንደር ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች ተጎጂ ወገኖችን ለማፅናናት ጎንደር ገቡ
ጎንደር፣ ግንቦት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋምት ጉባኤ አመራሮች በጎንደር ከተማ ተከስቶ በነበረው ግጭት የተጎዱ ወገኖችን ለማፅናናት ጎንደር ከተማ ገቡ።
የጉባኤው አመራሮች የሰባት ቤተ እምነት ተወካዮችን ያካተተ መሆኑንና በዛሬው ፕሮግራም የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውረው በመመልከት የተጎዱ ወገኖችን እንደሚያጽናኑ ይጠበቃል።
ነገ ደግሞ ከከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገልጸዋል።
የጉባኤው አመራር አባላትን በአፄ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘትም የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎንደር ከተማ ሰላምና ልማት ሸንጎ አባላት አቀባበል አድርገውላቸዋል።