የሱዳን አብዮታዊ ግንባር በተመድና በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት በሀገሪቱ የሚካሄደውን ብሔራዊ ምክክር እንደሚቀበለው አስታወቀ

192

ግንቦት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሱዳን በአጋር አካላት አማካኝነት የአስቸኳይ አዋጁን ለማንሳት፣ የፖለቲካ እስረኞችን ለመልቀቅና የዜጎችን ነጻነት ለመጠበቅ የሚደረገው እንቅስቀሴ ለብሔራዊ ምክክሩ መልካም ሁኔታ መፍጠሩ ተነግሯል።

በዚህም የኦማር አልበሽርን መንግስት በመቃወም የተመሰረተው የሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ታጣቂ ቡድኖች ጥምረት የሱዳን አብዮታዊ ግንባር (ኤስአርኤፍ) በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ የሚደረገውን ብሔራዊ ምክክር እንደሚቀበለው አስታውቋል።

ብሔራዊ ምክክሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በአፍሪካ ሕብረትና በኢጋድ አመቻችነት የሚካሄድ ሲሆን የግንባሩ መሪዎች ከአመቻቾቹ ተወካዮች ጋር መምከራቸው ተነግሯል።

የሱዳን አብዮታዊ ግንባር (ኤስአርኤፍ) እ.አ.አ በ2011 የተመሰረተ ጥምረት ሲሆን በሀገሪቱ አሉ ከሚባሉ የፖለቲካ ሃይሎች አንዱ መሆኑን ቲአርቲ ወርልድ ዘግቧል።

የቀድሞ የሱዳን ሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት አብደላ ሃምዶክ ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ በሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል ውጥረት መፈጠሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም