ስለ ጎንደር ከተማ በሩቅ ሆነን የሰማነው የተጋነነ ወሬና እዚህ መጥተን የተመለከትነው ፍጹም ተቃራኒ ነው-የጎንደር ዩንቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች

ግንቦት 1 ቀን 2014 (ኢዜአ) ስለ ጎንደር ከተማ በሩቅ ሆነን የሰማነው የተጋነነ ወሬና እዚህ መጥተን የተመለከትነው ፍጹም ተቃራኒ ነው ሲሉ የጎንደር ዩንቨርሲቲ የተቀበላቸው አዲስ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ተናገሩ፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ ለዘንድሮ የትምህርት ዘመን ትምህርት ሚኒስቴር የመደበለትን 5 ሺ 337 አዲስ ተማሪዎች ዛሬ መቀበል ጀምሯል፡፡

''ጎንደር እንደሚወራው አይደለም ፍጹም ሰላምና ህዝቡም እንግዳ ተቀባይ መሆኑን በአካል ተገኝቼ ተመልክቻለሁ ''ያለችው ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የመጣችው ተማሪ ቤተልሄም ፍቃዱ ነች፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአዲስ ተማሪዎች አቀባበል ደስ የሚልና ወደ ሁለተኛ ቤቴ እንደመጣሁ እንዲሰማኝ አድርጎኛል ያለችው ተማሪ ቤተልሄም ለትምህርቷ ትኩረት በመስጠት አላማዋን ለማሳካት ዝግጅት አድርጋ መምጣቷን ተናግራለች፡፡

ከቦረና ዞን ተከላላ ወረዳ የመጣችው ተማሪ ታምሬ እንድሪስ በበኩሏ ስለ ጎንደር ከሰሞኑ የተወራው የተጋነነ ወሬ እኔም ሆንኩ ወላጆቼ ደፍረን ለመምጣት ስጋት አድሮብን ነበር ብላለች፡፡

ሆኖም ጎንደር ከደረስኩ በኋላ ተዘዋውሬ የተመለከትኩት ሁኔታ ፍጹም ተቃራኒና ጎንደር ሰላምና ህዝቡም በእለት ተእለት ተግባሩ ተሰማርቶ ሲንቀሳቀስ ማስተዋሏን ተናግራለች፡፡

ከኢሉባቦር ዞን ያዩ ወረዳ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመደበ ልጃቸውን ይዘው የመጡት አቶ አህመድ እንድሪስ ስለ ጎንደር የሚወራው ወሬ እና እዚህ በአካል መጥቼ የተመለከትኩት እጅግ ተቃራኒ ነው ብለዋል፡፡

ጎንደር ቀድሞም ቢሆን ወደ አካባቢው ለሚመጡ እንግዶች መልካም መስተንግዶ የሚያደርግ ኢትዮጵያዊ ባህል ያለው ኩሩ ህዝብ በመሆኑ ልጄን ለዩንቨርሲቲውና ለከተማው ህዝብ በሰላም አስረክቤ ለመመለስ ዝግጁ ነኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ ጎንደር ዩንቨርሲቲ የተመደበች ልጃቸውን ይዘው የመጡት አቶ ዘሪሁን ገረመው የጎንደር ህዝብ እንግዳ ተቀባይ እንዲሁም ሰላም ፈላጊ መሆኑን ዛሬም በአካል ተገኝቼ ያረጋገጥኩት ይህንኑ ነው ብለዋል፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ምክትል ፕሬዘዳንት ተማሪ እሱባለው ውቤ ህብረቱ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ዩኒቨርሲቲው ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት አዲስ ተማሪዎችን እያስተናገድን ነው ሲል ተናግሯል፡፡

ወደ ዩንቨርሲቲው የሚመጡ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ተሽከርካሪዎችን በመመደብ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡለት 5ሺ 337 አዲስ ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ካምፓሶች ከዛሬ ጀምሮ መቀበል መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

አንጋፋው የጎንደር ዩንቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በመደበኛው በማታውና በክረምት የትምህርት መርሃ ግብሮች ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ባሉ የትምህርት እርከኖች ከ40ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም