ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ሰባት ሜዳሊያዎችን አገኘች

ግንቦት 1/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ሲካሄድ በቆየው የምሥራቅ አፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሰባት ሜዳሊያዎችን በማግኘት አጠናቃለች።

ከሚያዚያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ዘጠኝ አገራት የተሳተፉበት ውድድር ለአራት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተካሂዷል።

በዚህ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ብሄራዊ ቡድን ሰባት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችሏል።

ከሰባቱ ሜዳሊያዎች ሁለት የወርቅ፣ ሁለት የብር እና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ነው ኢትዮጵያ ያገኘችው።

የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ በወንዶች የነጠላ ውድድር በአትሌት ደራራ መኮንን የተገኘ ሲሆን፤ ሁለተኛው የወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ በሴቶች የቡድን ጨዋታ የተገኘ ነው።

ሁለቱ የብር ሜዳሊያዎች ደግሞ በሴቶች ነጠላ ውድድር ማርታ መሸሻ እና በወንዶች የቡድን ጨዋታ የተገኙ ናቸው።

ሦስቱ የነሐስ ሜዳሊያዎች ደግሞ በሴቶች ነጠላ ውድድር በሜሮን ጌታነህ እና በቤተልሔም ሲሳይ አማካኝነት  የተገኙ ሲሆን፤ ሌላኛው አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ደግሞ በወንዶች የነጠላ ውድድር በአትሌት ኤደን ተስፋዬ  የመጣ ነው።

በዚህ ውድድር ጥሩ ተፎካካሪ የነበሩት የሞሪሽየስ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ሁለት ወርቅና ሁለት የብር ሜዳሊያ ማግኘት ችለዋል።

በውድድሩ በቡድን ሁለት ሀገራት፤ በነጠላ ደግሞ ከአንድ እስከ ስምንተኛ ደረጃ የወጡ ስፖርተኞች ምሥራቅ አፍሪካን ወክለው በ2022 ዓ.ም በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ውድድር ላይ የሚካፈሉ ይሆናል።

በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ በቡድን ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር በሁለቱም ጾታ ተካፋይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በነጠላ ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድርም በሴቶች አምስት፤ በወንዶች ደግሞ አራት ስፖርተኞች መሳተፍ እንደሚችሉ ተረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ብዛኔ ኢትዮጵያ ይህን ውድድር በተሳካ መልኩ ማስተናገዷን ገልጸዋል።

በዚህ ውድድር የተካፈሉ ኢትዮጵያዊያን ስፖርተኞችም ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን አመርቂ ውጤት እንዳስመዘገቡ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም