ቀጥታ፡

የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በመከበር ላይ ነው

ግንቦት 1 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን "ጋዜጠኝነት በዲጂታል ዓለም ውስጥ " በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው።

በመርሓ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ፣ አንጋፋ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች በመሣተፍ ላይ ይገኛሉ።

መርሃ ግብሩን በንግግር ያስጀመሩት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሰብሳቢ ጋዜጠኛ አማረ አረጋዊ፤ ጋዜጠኞች የሚዲያ ነጻነትን ለድርድር ሳያቀርቡ ስራቸውን ስነ-ምግባር ባለው መልኩ ማከናወን አለባቸው ብለዋል።

''በአሁኑ ጊዜ የዲጂታል ሚዲያው በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል'' ያሉት ጋዜጠኛ አማረ፤ ዘርፉን ለአገር በሚበጅና የህዝቦችን አንድነት በሚያስቀጥል መልኩ መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ዕለቱ ታስቦ መዋሉ ሃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ ባለሙያ እንዲኖር ከማድረግ አንጻር ትላቅ አስተዋጽኦ አለውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ ባደረጉት ንግግርም ከለውጡ ወዲህ መንግስት መረጃን ተደራሽ ለማድረግ መገናኛ ብዙኃን እንዲስፋፉና እንዲጠናከሩ ለማድረግ የፖሊስ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙኃን የሙያ ማህበራት እንዲስፋፉ መደረጉንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ዜጎች ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ ለማድርግ ባለስልጣኑ ሃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩም ዲጂታል ሚዲያው ስነ-ምግባር ባለው መልኩ ስራውን እንዲወጣ የሚያደርግ ዓላማ ያለው ውይይት የሚካሄድ ይሆናልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም