የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የህዝቦቿን ህልውና በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የሚችል የመከላከያ ሰራዊት ገንብተናል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የህዝቦቿን ህልውና በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የሚችል የመከላከያ ሰራዊት ገንብተናል
ግንቦት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የህዝቦቿን ህልውና በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የሚችል የመከላከያ ሰራዊት ገንብተናል ሲሉ የምዕራብ ግንባር ዋና አዛዥ ጀነራል ጌታቸው ጉዲና ገለጹ።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በስልጣን ላይ በቆየበት ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ የመከላከያ ሰራዊቱን በአንድ ፓርቲ የበላይነት ማደራጀቱ ይታወቃል፡፡
በዚህም ሰራዊቱ ገለልተኛ ሆኖ ኢትዮጵያን ከማገልገል ይልቅ "አብዮታዊ ዲሞክራሲ" የሚለውን አንባገነናዊ የፓርቲ ስርዓት ለማስጠበቅ ሲጠቀምበት ቆይቷል፡፡
የሽብር ቡድኑ ይህ አልበቃ ብሎት በሰሜን እዝ አባላት ላይ ጥቃት በመክፈት ታሪክ ይቅር የማይለው የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽሟል፡፡
የምዕራብ ግንባር ዋና አዛዥ ጀነራል ጌታቸው ጉዲና ለኢዜአ እንዳሉት፤ በሰራዊቱ አደረጃጀት ውስጥ ከፍተኛው አመራርና ስታፍ ድርሻ በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ብቻ ተይዞ ነበር።
"በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" እንዲሉ እነዚሁ አመራሮች እርስ በርስ ተናበው ሰራዊቱ ላይ ጦርነት በመክፈት አገርን ያለ ጠባቂ ለማስቀረት ከፍተኛ ሴራ መፈጸማቸውን አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሰራዊቱ በእልህና ቁጭት በመዋጋት ሴራቸውን ከማክሸፍ ባለፈ በኢትዮጵያን ህልውና ላይ ተደቅኖ የነበረውን አደጋ መመከት ችሏል ነው ያሉት፡፡
ከህልውና ዘመቻው በኋላ በየደረጃ ላለው የሰራዊት አባል በቂ ወታደራዊ ስልጠና መሰጠቱን የገለጹት ጀነራል ጌታቸው፤ በዚህም ኢትዮጵያን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላት መጠበቅ በሚያስችል ሙሉ ቁመና ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በማንኛውም የመሬት ገጽና የአየር ጸባይ የውጊያ አውዱ የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግ የሚችል ጠንካራ ሰራዊት መገንባቱንም ጨምረው ገልጸዋል።
ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ህልውና ለመድፈር የሚሞክር የትኛውንም ኃይል በአስተማማኝ ሁኔታ መመከት በሚያስችል ዝግጁነት ላይ መሆኑንም ነው አጽኖት ሰጥተው የተናገሩት፡፡