ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በዘላቂነት ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2010 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰፋት የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዘላቂነት እንዲቀጥል ኢዜአ ያነጋጋራቸው የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማህበራት አመራሮች ጠየቁ። በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ እርስ በርስ የመረዳዳት ባህልን እንዳነቃቃም ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2011 በጀትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ዜጎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ለአገራቸው ዕድገት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ጥሪውን ተከትሎ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች በመሳተፍ መንግስት ሊያወጣ የነበረውን ካፒታል ከማስቀረታቸውም በላይ ኢትዮጵያውያን ይታወቁበት የነበረውን እርስ በርስ የመደጋጋፍ ባህል እንዲዳብር አዎንታዊ ሚና ተጫውተዋል። የ'ቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ'(ቪኮድ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ እንዳሉት በርካታ ያደጉ አገራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በሚገባ የተጠቀሙበት ሲሆን በኢትዮጵያም ተጀምሮ የሚጠፋ ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ መሆን አለበት ብለዋል። የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ህብረት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ በበኩላቸው በዜጎች ላይ ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ብቻ የሚፈታ ሳይሆን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጭምር በመሆኑ የተጀመረው ተግባር ባህል ሆኖ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል። ተግባራቱ አንዴ ታይተው የሚጠፉ እንዳይሆኑ በየዓመቱ የተወሰኑ ቀናቶችን መርጦ ለመሰል ተግባር እንዲሆኑ መለየት እንደሚገባም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ በጎ አድራጎትና ሲቪክ ማህበራት መድረክ ሊቀመንበር አቶ ተክሉ ነጋሽ እንዳሉት፤ የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማህበራት በሚገባ የተደራጁ ባለመሆኑ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። በመሆኑም ማህበራቱ ያለባቸውን ክፍተት በማስተካከል በቀጣይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን በመሪነት ለመተግበር መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል። እያንዳንዱ ዜጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ ተረድቶ በዘላቂነት ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 3 ሺህ 1 መቶ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም