የአምስቱ አጎራባች ክልሎች የባህል ዐውደ ርዕይ በሐረር ከተማ ተከፈተ

36

ሐረር ሚያዝያ 30/2014(ኢዜአ)...በሐረሪ ክልል የሚከበረው የሹዋል ኢድ አካል የሆነው የአምስቱ አጎራባች ክልሎች የባህል ዐውደ ርዕይ በሐረር ከተማ ተከፈተ ።

ዐውደ ርዕዩን የከፈቱት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ  ኦርዲን በድሪ ናቸው።

የዘንድሮው የሐረሪ ክልል 1ሺህ 443ኛ የሹዋል ኢድ በዓል "ከኢድ እስከ ኢድ" በሚል መርሃ ግብር በተለያየ ዝግጅት ዛሬ በደማቅ ሥነስርዓት መከበር ጀምሯል።

እንዲሁም የመርሃ ግብሩ አንድ አካል  የሆነው የአምሰቱ  አጎራባች ክልሎች የባህል ዐውደ ርዕይ ለእይታ ክፍት ሆኗል።

አምስቱ አጎራባች ክልሎች በክብረ በዓሉ ላይ የየክልላቸውን ባህል የሚያንፀባርቁ አልባሳትና ቁሳቁስ በመያዝ ተሳትፈዋል፡፡

የሶማሌ ክልልን በመወከል  የተሳተፉት  አቶ አብዲ መሐመድ ይህን መሰል የጋራ መድረክ መካሄዱ  እርስ በርስ ለመተዋወቅ ያስችለናል ብለዋል።

በኅብረተሰቡ መካከል አንድነትን ከመፍጠሩ ባለፈ አንዱ ከሌላው የእርስ በርስ ልምድና እውቀት የሚገበያይበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የሹዋል ኢድ ከወትሮው በተለየና ባማረ ሁኔታ እየተከበረ መሆኑን የሐረሪ የባህል አልባሳትና ቁሳቁስ በዐውደ ርእዩ ላይ ይዘው የቀረቡት የሐረሪ ማህበረሰብ የባህል አልባሳት  ባለሙያ አቶ አብዱላሂ ሙሴ ገልጸዋል፡፡

ዐውደ ርዕይው ሁሉም ያለውን የእደ ጥበብ ሙያና የባህል ቁሳቁስ አውጥቶ የሚያሳይበትና ባህሉን የሚያስተዋውቅበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ሚስራ አብዱረህማን  ሌላኛዋ የባህል ዐውደ ርዕዩ ተሳታፊ ሲሆኑ፣ ሐረር ላይ የብሄሮች አንድነትና አብሮነት ተለመደ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ዐውደ ርዕዩን ''እርስ በእርስ ያለንን ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክርና ባህላችንን እርስ በእርስ የምንለዋወጥበት መድረክ ነው''ብለውታል፡፡

የድሬደዋ አስተዳደርን በመወከል የተሳተፉት ወይዘሮ ሰብለ ፀጋዬ  የተለያዩ ብሄረሰቦች ባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁስ ይዘው መምጣታውን ተናግረዋል፡፡

ዐውደ ርዕዩ ''የማይተዋወቁ እርስ በርስ የሚተዋወቁበት፤ የተለያየን ለምንመስላቸው አንድነታችንን የምናሳይበት መድረክ ነው'' ብለዋል ፡፡

በዚሁ በአምስቱ  አጎራባች ክልሎች የባህል ዐውደ ርዕይ መክፈቻ ላይ "ከኢድ እስከ ኢድ" ጉዞ ጣምራ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዑስታዝ አቡበከር አህመድን  ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም