የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የተፈጥሮ ሃብታቸውን በጋራና በትብብር መጠቀም አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የተፈጥሮ ሃብታቸውን በጋራና በትብብር መጠቀም አለባቸው
ሚያዚያ 30/2014/ኢዜአ/ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ያላቸውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በጋራና በትብብር መጠቀም እንዳለባቸው የአገራቱ ምሁራን አስገነዘቡ።
"ፒፕል ቱ ፒፕል" በተሰኘ አለም አቀፍ ድርጅት አዘጋጅነት የአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ ፈተናዎች፣ መልካም እድሎችና አካባቢያዊ ትብበር ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲሰ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚው መስፍን ጣሰው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ እንዲሁም በአለም በትብብር በመስራት ያስመዘገባቸውን ስኬቶች አብራርተዋል።
አየር መንገዱ ባለፉት አመታት የአየር መንገድ ትስስር አገልግሎት በመስጠት ለአፍሪካ ማህበራዊና ምጣኔሃብት ልማት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት 45 የአፍሪካ አገሮችን በመድረስ አፍሪካን ወደ አንድ ማምጣት የሚለውን መሪ ሃሳብ በመሪነት እየተጫወተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የካርጎ፣ የንግድ፣ የቱሪዝም ኮንፈረንስና ለሌሎች ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴን በትጋት እንደሚሰራ ጨምረዋል።
የአፍሪካ ቀንድ አገራት ሃብትን በትብበር ከመጠቀም አኳያ ክፍተት እንዳለ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት 80 በመቶ የአፍሪካ ተጓዦች የአፍሪካ ባልሆኑት አየር መንገዶች እንደሚጠቀሙ በማሳያነት አንስተዋል።
በቀጠናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር በትብብርና በጋራ መስራት ከተቻለ ስኬት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሞክሮ ጥሩ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
ከጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ በውይይቱ ለመሳተፍ የመጡ ምሁራን የአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ ፈተናዎች፣መልካም እድሎችና አካባቢያዊ ትብበር መስኮችን ዘርዝረዋል።
የአፍሪካ ቀንድ በከፋ ድህነትና ኋላቀርነት፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በእርስ በእርስ ጦርነት፣ መፈናቀል፣ ድርቅ፣ በሽታና ሌሎች ችግሮች ውስጥ መሆኑን ምሁራኑ ዘርዝረዋል።
በደቡብ ሱዳን ጁባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ፣ ሰላምና ጸጥታ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አብርሃም ልኡል በአፍሪካ ቀንድ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ለሰላምና አለመረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የጋራ ራዕይና አላማ በመያዝ፣ የተፈጥሮ ሃብቶችን በማልማትና ቀጣናዊ ችግሮችን በትብብር በመፍታት የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ያነሱት ደግሞ በኤርትራ የስትራቴጂክ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ ዶክተር ፍቅረእየሱስ አምሃ ጺዮን ናቸው።
የጅቡቲ የወደብ አማካሪ ዶክተር መውሊድ አደን፤ በቀጣናው ያሉትን ወጣቶች እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዋነኛ የልማት አጋር ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በአፍሪካ አወንታዊ ውድድርን በማጎልበትና የጋራ ብልጽግናን በማስቀደም ለዜጎቿ የተሻለች አህጉርን መፍጠር መሪዎች ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም ምሁራኑ ጠቁመዋል።