አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ ወደ ስራ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ ወደ ስራ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን ወጣቶች ገለጹ
አዲስ አበባ ጳግሜ 2/2010 አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ ወደ ስራ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ገለጹ። በኢትዮጵያ በተጀመረው የመደመር፣ የፍቅርና የአንድነት አመት የበኩላቸውን ለማበርከት እንደሚሰሩም ተናግረዋል። ወጣቶቹ አሁን በተገኘው የለውጥ እንቅንቃሴ ውስጥ የራሳቸውን ስራ ፈጥሮ ለመስራት እንደሚፈለጉ ነው የተናገሩት። አሁን ያለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅቶ ለመስራት ፍላጎትና መነሳሳት እንደፈጠረባቸው በማውሳት። አስተያየታቸውን ከሰጡት ወጣቶች መካከል ሙሉጌታ ደሳለኝ " አሁን ያለውን ለውጥ በአዲሱ አመት ከመንግስት ና ከህዝባችን ጋር ለማስቀጠል የበኩሉን ለመወጣት መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡ ወጣቶች በተግባር ወደ ስራ መግባት አለባቸው ከቃላት ንግግር በተጨማሪ አዲሱን ዓመትም በሰላ እንዲሆን የበኩሉን ለማበርከት እንደሚሰራ የገለጸው ደግሞ ወጣት መላኩ ጉዳታነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም ለማስጠበቅም በአገሪቱ የተረጋጋ ሰላም እንዲኖር ወጣቱ ዘብ መቆም እንዳለበት ይናገራሉ እነዚሁ ወጣቶች። ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ያሉት የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችም በመንግስት መፈታት እንዳለበት እያሳሰቡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ወጣቶችን ከማደራጀት በተጨማሪ በአግባቡ መደገፍ እንደሚገባቸው ይናገራሉ። በዚህም ወጣቱ ለራሱም ሆነ ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን መወጣት እንደሚቻለው በመተማመን። "ወጣቱ ላይ ያሉ ችግሮች መደራጀት ይደራጃል፣ አደራጅ አይጠፋም፣ ከተደራጁ በኋላ ግን የሚሰሩ ስራዎችን ተከታትሎ ከማስፈጸምና የተደራጁ ወጣቶችን የት እንዳሉ የሚከታተል አካል የለም።” የሚለው ወጣት ሙሉጌታ ደሳለኝ ነው፡፡ ወጣት ቢኒያም ደምሴ በበኩሉ ወጣቱን በአዲሱ መንፈስ ማነሳሳት ና የማደራጀት አቅሙ ካለ የበለጠ ነገር መስራት ይቻላል ባይ ነው፡፡ ወጣቱ አሁን ያለው አገራዊ መነቃቃት የፈጠረላቸውን መነሳሳት ይዘው ወደ ስራ ቢገቡ ለኢትዮጵያ ዕድገት የበኩላቸውን ማበርከት እንደሚያስችላቸው የሚናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ ናቸው። እንደ አቶ ሚኪያስ ገለጻ ለአብነትም በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ ለወጣቶቹ ጥያቄ ምላሽ ሊሰጡ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በአዲሱ 2011 በጀት ዓመት በዘርፉ የሚታየውን ችግሮች ለመቅርፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በተቋሙ ችግር ያለባቸውን አሰራሮች ለመቅረፍም ከላይ እስከ ታችኛው አመራር የማደራጀት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። የፋይናንስ ችግር ለማቅረፍ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም እና ከአዲስ ከፒታል ጋር በመሆን እየተንቀሳቀስን እንገኛለንም ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለከተማዋ የተመደበ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ስላለ የፋይንናስ ችግር እንደሌለ ጠቁመዋል።