ጥልቅ አሳቢና ሩቅ አላሚ ትውልድ ለመፍጠር የንባብ ባህልን ማዳበር ላይ በትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
ጥልቅ አሳቢና ሩቅ አላሚ ትውልድ ለመፍጠር የንባብ ባህልን ማዳበር ላይ በትኩረት ይሰራል
ጎባ፤ ሚያዚያ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጥልቅ አሳቢና ሩቅ አላሚ ትውልድ ለመፍጠር የንባብ ባህልን ማዳበር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሃፍት አገልግሎት ገለጸ።
የትውልድን የንባብ ባህል ለማሳደግ ዓላማ ያደረገው የንባብ ንቅናቄ ሳምንት መረሃ ግብር በባሌ ዞን ሮቤና ጎባ ከተሞች "መፅሓፍት የዕውቀት ምንጭ ጮራ፣መዛግብት የታሪክ አሻራ "በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ተጀምሯል።
መረሃ ግብሩ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሃፍት አገልግሎት ከኦሮሚያ ክልል፣ ከባሌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤትና መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መሆኑ ተገልጿል።
የንባብ ሳምንት መድረኩን የከፈቱት የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሃፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ የኩኑአምላክ መዝገቡ እንደገለጹት ጥልቅ አሳቢና ሩቅ አላሚ ትውልድ ለመፍጠር የንባብ ባህል ማዳበር ይገባል።
ተቋማቸው መጽሃፍትን በማሰባሰብና በማደራጀት በንባብ ባህል ዙሪያ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጥናትና ምርምር ተደራሽ ለማድረግ እየሰረ መሆኑን ተናግረዋል። ከአገሪቱ መሃል ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች የሚሰተዋሉ የመጽሃፍት እጥረት ተደራሽ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ዋና ዳይረክተሩ የተናገሩት።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በባሌ ዞን የተካሄደው የንባብ ሳምንት መድረክ የትውልድን የንባብ ባህል ለማሳደግ ዓላማ ከማድረጉም በተጨማሪ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መጽሃፍት ድጋፍ የተደረገበት ነው ብሏል።
ተቋሙ ለዞኑ ያደረገው የንባብና ሌሎች የማጣቀሻ መጽሃፍት ድጋፍ በተለያዩ አርዕስቶች ላይ የተጻፉና ለ15 ቤተ-መጽሃፍት የሚውሉ እንደሆነ ተናግረዋል። የባሌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ሮብዳ ጃርሶ በበኩላቸው የትውልድን የንባብ ባህል በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለሚያበረክተው መርሃግብር ተቋሙን አመስግነዋል።
በተለይ የተደረገላቸው የመጽሃፍት ድጋፍ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ከሚኖረው አስተዋጽኦ በተጓዳኝ ያለባቸውን ውስንነት ለመቅረፍ ያግዛል ነው ያሉት።
በመርሃግብሩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ደራሲያን መካከል አቶ መሀመድ አሚን በሰጡት አስተያየት መሰል መርሃ-ግብሮች መዘጋጀታቸው በንባብ ባህል የዳበረና በምክንያታዊነት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 2 /2014ዓ.ም. በሚቆየው የንባብ ንቅናቄው ሳምንት መረሃ ግብር ላይ አንባቢያን፣ተማሪዎች፣ ደራሲያንና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጽሃፍት አገልግሎት የመዛግብት፣የጽሁፍ ቅርሶችና ህትመቶችን በማሰባሰብና በማደረጀት ለአገልግሎት ማቅረብ ብሎም ለትውልድ እንዲያስተላልፍ ታስቦ በ1936 ዓ ም መቋቋሙ ታውቋል።