የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር ጀግና ሰራዊት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ሚያዚያ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር ጀግና ሰራዊት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምዕራብ ግንባር የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴን በሁመራ ተገኝተው ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰላም ሲደፈርስ መመለስ የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳለ አረጋግጠናል ብለዋል።

ሰራዊቱ እንደ ተኩላ በህብረት የሚያጠቃ እንደ አንበሳ ቦታውን የማያስደፍር ጀግና መሆኑንም ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ በሆኑ ሰባት ወታደራዊ ሳይንስ መመዘኛ መስፈርቶች መሰረት ጀግና መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።

ሰራዊቱ ድል የሚፈጥር፣ ሞትን የሚያሸንፍ፣ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር፣ ፍላጎቱን ለአላማው የሚያስገዛ፣ የነፃነትን ዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ጨለማን ማሻገር የሚችል ሞራልና ጉልበት ያለው፣ በልማትና በጥፋት መካከል የማይፈርስ ጠንካራ ግንብ መሆኑን ጠቁመዋል።

ግልፍተኝነት፣ ያልተገባ ክብር መፈለግ፣ ስሱነት ወይም በጥቂት ድል መርካት እንዲሁም ከልክ ያለፈ ፍርሃት ጀግንነቱን እንዳያበላሹበት መጠንቀቅ ይገባል ብለዋል።

የምዕራብ ግንባር ዋና አዛዥ ጀነራል ጌታቸው ጉዲና በበኩላቸው የግንባሩ ሰራዊት ከህልውና ዘመቻው በኋላ የነበሩትን ክፍተቶች በመሙላት የተስተካከለ የውጊያ ቁመና ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰራዊቱን በማሰልጠን የተደራጀ የመከላከልና ጸረ ማጥቃት አቅም መገንባቱንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ የምትፈልገውን አይነት ሰራዊት ገንብተን ለማሳየት ትጋት ቁርጠኝነት አይለየንም ብለዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም