ቀጥታ፡

የአባይ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 61 ነጥብ 5 በመቶ ደርሷል

ሚያዝያ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያቶች መስተጓጎል ፈጥሮበታል የተባለው አዲሱ የአባይ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 61 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱ ተገለጸ።

ግብአቶች አቅርቦት በሚፈለገው መጠን አለመሆን የግንባታው ሂደት ላይ ተጽእኖ አሳድሯልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የሚሰሩና የሚመሩ መሐንዲሶች በባህርዳር ከተማ እየተገነባ ያለውን አዲሱ የአባይ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት ዛሬ ጎብኝተዋል።

በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ የአባይ ድልድይ ግንባታ መካሄድ የጀመረው በ2011 ዓ.ም ሲሆን፤ የድልድዩ ግንባታ ያስፈለገው በ1953 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የተገነባው ነባሩ የአባይ ድልድይ አማራጭ እንዲሆን ነው።

የድልድዩ ግንባታ ፕሮጀክት ምክትል ተጠሪ ኢንጂነር ፍቅረስላሴ ወርቁ ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመትና 43 ሜትር የጎን ስፋት ያለውና የባህርዳር ከተማን ቀጣይ እድገትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ድልድዩ በአንድ ጊዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ማስተላለፍ የሚችል ባለሁለት አካፋይ ያለውና አምስት ሜትር የሳይክልና የእግረኞች መንገድ ያካተተ ነው።

በተጨማሪም የትራፊክ ምልክቶች፣የድልድይ ላይ መብራቶች፣የተሽከርካሪ መውጫና ሌሎች የኮንክሪት መዋቅሮችን ይዟል።

እንደ ኢንጂነር ፍቅረስላሴ ገለጻ፤ በ2011 ዓ.ም የተጀመረው ፕሮጀክት በ2013 ዓ.ም መጨረሻ መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም እስካሁን ያለው የግንባታ አፈጻጸም 61 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ ነው።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በጦርነት ምክንያቶች በግንባታ ግብአቶች አቅርቦት ላይ ጫና በመፍጠሩ ፕሮጀክቱን በተባለው ጊዜ ማጠናቀቅ አለመቻሉን ተናግረዋል።

የግብአት አቅርቦቶች በሚፈለገው መጠን ከተሟሉ ፕሮጀክቱን በ2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙንና ለዚህም አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ ምክትል የፕሮጀክቱ ተጠሪ ጠይቀዋል።

የቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ(ሲሲሲሲ) የአባይ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታ ተቋራጭ ሲሆን፤የቱርኩ ስታዲያ ኢንጅነሪንግ ወርክስ ኮንሰልታንት ድርጅት የፕሮጀክቱ አማካሪ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም