ሃገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ የምሁራን ውይይት በአሶሳ ዩኒቨርስቲ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ሃገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ የምሁራን ውይይት በአሶሳ ዩኒቨርስቲ ተጀመረ
ሚያዚያ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሃገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ የምሁራን ውይይት በአሶሳ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ ነው።
"ብሄራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንጻር የምሁራን ሚና" በሚል መሪቃል በሚካሄደው በዚሁ መድረክ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ተማሪዎችና ሌሎች አካላት እየተሳተፉ ነው።
በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሄራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር “ ኢትዮጵያ እንቆቅልሽ በሚመስል መልኩ ለገጠማት ችግር መፍትሄው ውይይት ብቻ ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ረጅም አመት ቢሆነውም የእድሜውን ያህል አይደለም ሲሉ የገለጹት ሚኒስትር ዴታው የዚህም ምክንያቱ የተቋማት አለመጠናከር እና የሃገሪቱ ልሂቃን መካከል መሰረታዊ መግባባት አለመኖር ነው ሲሉ አመልክተዋል።
ሃገራዊ ምክክሩ መፍትሄ እንደሚሰጥ ይጠበቃል ያሉት አቶ ታዬ ምሁራን ሚናቸውን እየተወጡ ስለመሆኑ ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው ሲሉ አስረድተዋል።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም በውይይት እና በምክክር ሰላማዊ ሃገር ለልጆቻችን ማስተላለፍ ያስችላል ብለዋል።
የውይይት መድረኩ ዓላማ በሃገራዊ ጉዳዮች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አስተዋጽኦ ለማበርከት ያለመ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በክልሉ የተፈጥሮ ሀብት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን አስረድተው ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ተፈናቃዮችን ከመደገፍ ጀምሮ ለሰላም መጠናከር ድርሻውን እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
የውይይት መድረኩን የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ እና በሰላም ሚኒስቴር በጋራ እንዳዘጋጁት ታውቋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ