ቀጥታ፡

ወጣቶች ባልታወቀና ባልተረጋገጠ ጉዳይ ወደ ግጭትና ረብሻ ከመሔድ ይልቅ የጉዳዩን ምንነት መመርመር አለባቸው

ሚያዚያ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ወጣቶች ባልታወቀና ባልተረጋገጠ ጉዳይ ወደ ግጭትና ረብሻ ከመሔድ ይልቅ የጉዳዩን ምንነት መመርመር እንዳለባቸው የኃይማኖት አባቶች መከሩ።

የኃይማኖት አባቶቹ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ስነ-መለኮት ድሕረ ምረቃ ትምህርት ቤት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ባከበረበት ወቅት ነው።

የኃይማኖት አባቶቹ እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መነሻቸውና ምንነታቸው ያልተረጋገጡ ጉዳዮች ወደ ረብሻ እያደጉ ነው ።

ለዚህ ደግሞ በዋናነት ሰለባ እየሆኑ ያሉት ወጣቶች መሆናቸውን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ወጣቶች ነገሮችን በሰከነ መንፈስ መመርመር እንዳለባቸው ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ቄስና የኢትዮጵያ ስነ-መለኮት ድሕረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ቄስ ዶክተር ምስጋና ማቲዎስ፡  ከሁሉም በላይ ትዕግስት ይቀድማል ብለዋል።

የትኛውም ኃይማኖት መሰረቱ ሰላምና አብሮነት መሆኑን የጠቀሱት ቄስ ዶክተር ምስጋና አብዛኛው አማኝ በሆነባት አገር እነዚህ ሁለቱ ሊጓደሉ አይገባም ነው ያሉት።

በየትኛውም መስፈርት ኢትዮጵያውያን በኃይማኖት ምክንያት እርስበርስ ተጋጭተው እንደማያውቁ ታሪክ ምስክር ነው ብለዋል።

ዋናው ችግር 'ላይ ላዩን' ኃይማኖት አስመሰለው ሌላ አጀንዳ የሚያስፈጽሙ አካላት የሚሰሩት ሴራ አለ ብለው እንደሚያምኑም ጠቅሰዋል።

በተለይም ወጣቱ በትንሹም በትልቁም ወደ ረብሻና ግጭት ከመግባት ይልቅ የጉዳዩን ምንነት መመርመር አለበት ሲሉም መክረዋል።

እርሳቸው በዳይሬክተርነት የሚመሩት የኢትዮጵያ ስነ-መለኮት ድሕረ ምረቃ ትምህርት ቤት በሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት ዙሪያ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ሊሰጥ ዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሌሎችም የትምህርት ተቋማት መሰል የትምህርት ዘርፎች ላይ አተኩረው ትውልዱን ማሻገር አለባቸው ብለዋል።

ሌላው የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶም፣ በዚህ ወቅት መረጋጋትና መስከን ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ።

ወጣቶች በየማሕበራዊ ሚዲያዎች ለገቢ ማግኛ ተብሎ የሚለቀቁ አጥፊ መረጃዎችን በሙሉ ከመቀበል ይልቅ በውስጡ የተደበቀውን አጀንዳ መመርመር አለባቸው ይላሉ።

በደፈናው ባልታወቀና ባልተረጋገጠ ነገር ተነስቶ ወደ ረብሻና ብጥብጥ መጓዝ ዘመኑን የማይመጥን አካሄድ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኃይማኖት አባቶችም ቢሆኑ የኃይማኖቱን ትዕዛዛት እያከበሩ ተግባራዊ ሕይወት ሊመሩ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

መንግስትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ አድሎና ልዩነት የሕግ የባላይነትን ለማስከበር ሊተጋ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ስነ-መለኮት ድሕረ ምረቃ ትምህርት ቤት በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ኃይማኖታዊና አለማዊ ትምህርቶችን እየሰጠ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ስነ-መለኮት ድሕረ ምረቃ ትምህርት ቤት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን መካነየሱስና በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት የተመሰረተ የትምህርት ተቋም ነውም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም