አካባቢያችንን ከጸረ ሰላም ኃይሎች እየጠበቅን ነው - ወጣቶች

አምቦ፣ሻሸመኔ ሚያዝያ 28/2014 (ኢዜአ) የራሳቸውን የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት ህዝቡን በብሄርና በሃይማኖት ለመከፋፈል ከሚጥሩ ጸረ ሰላም ሃይሎች አካባቢያችንን እየጠበቁ መሆናቸውን የምዕራብ ሸዋና የምዕራብ አርሲ ዞኖች ወጣቶች ተናገሩ፡፡

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚሰሩ ሀይሎች ወጣቱን መጠቀሚያ እንዳያደርጉ በንቃት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በምእራብ ሸዋ ዞን ከ22ቱም ወረዳዎች የተውጣጡ ወጣቶች ዛሬ  በአምቦ፣ የምዕራብ አርሲ ወጣቶች ደግሞ በሻሸመኔ ከተማ ከተማ ውይይት አድርገዋል።

በአምቦ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ የሜታ ሮቢ ወረዳ  ነዋሪ ወጣት ጌታሁን ገደፋ በሃይማኖት ሽፋንና በብሄር ከፋፍሎ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጸረ ሰላም ሀይሎች ላይ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፍ ተናግሯል፡፡

''አንድነታችንን አጠናክረን በትግል ያገኘነውን ለውጥ መጠበቅ አለብን''ብሏል፡፡

"የሀገርን ሰላም ማረጋገጥ የሚቻለው በመንግስት ብቻ ሳይሆን በኛ  የተባበረ ክንድ ነው" ያለው ደግሞ የሊበን ጃዊ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አብዲሳ ገለቱ ነው፡፡

ሀገር የጋራ በመሆኗ ሁላችንም ተደጋግፈንና ነቅተን ከተጋረጠባት አደጋ ልንታደጋት ይገባልዕ ሲል አክሏል፡፡

መንግሥት በሀይማኖት ሽፋን ግጭት በሚፈጥሩ አካላት ላይ ፈጣንና አስተማሪ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የገለጸው ደግሞ የዳኖ ወረዳ ነዋሪ ወጣት  አሸናፊ መንግስቱ ነው፡፡

"ወጣቶች እንደ ከዚህ በፊቱ አሁንም አንድነታችንን አስተባብረን ለሀገራችን ሰላም ከመንግስት ጎን በመሆን ለውጡን ለማስቀጠል እየሰራን ነው"ብሏል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የምእራብ ሸዋ ዞን  ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎሶምሳ ሀገራዊ ለውጡን ከማረጋገጥ ረገድ ወጣቶች በነበራቸው ሚና፣ ከለውጡ ጋር ተያይዞ እየታዩ ባሉ ተግዳሮቶችና በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ የመወያያ ጽሁፍ ጽሑፍ አቅርበዋል።

ውይይቱ የዞኑ ወጣቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ በቂ ግንዛቤ ጨብጠው በጸጥታ ማስከበር ሥራ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል አላማ ያደረገ መሆኑን  አስታውቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ ወጣቶች ለሀገር ሰላምና ግንባታ ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ወጣቶች ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልና የሀገር ሉዓላዊነት ተከብሮ እንዲቀጥል ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፤ አሁን ላይ በሀገር ላይ የተቃጣውን ሴራ ለማክሸፍ  በንቃት እንዲሳተፉ አስገንዝበዋል፡፡

የምእራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በበኩላቸው "ሀገርን ከገጠሟት ችግሮች ለመታደግ በወያኔ ሳምባ የሚተነፍሱ አሸባሪ ቡድኖችን ተባብረን እናጥፋ "ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ የምዕራብ አርሲ ዞን ወጣቶች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ውይይት በሀይማኖት ስም በመንቀሳቀስ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በንቃት እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስልታቸውን እየቀያየሩ ወጣቱን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ድርጊት በንቃት እየተከታተሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

መስሊምና ክርስቲያንን ለማጋጨት ላይ ታች የሚሉትን  ፀረ ስላም ኃይሎች በዞናቸው ስፍራ እንዳያገኙ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሐጂ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የዞኑ  ወጣቶች  በልማትና በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ንቁ ተሳታፊ ከመሆን በተጨማሪ የፀረ ሰላም ኃይሎችን  አፍራሽ እንቅስቃሴ እንዲያከሽፉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም