ዜጎች የጋራ እሴቶች ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን እንዲመክቱ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቀረቡ

31

ጭሮ ሚያዝያ 28/2014(ኢዜአ)- ዜጎች ቀድሞ በነበሩ የአብሮነትና አንድነት የጋራ እሴቶች ላይ እያጋጠሙ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እንዲመክቱ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን የሀይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቀረቡ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የዞኑ ሀይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉት ኢትዮጵያ የተጋመደ የአብሮነት ታሪክ፣ የተሰናሰለ የችግር አፈታት ስርዓቶችና የቆየ የጋራ እሴቶች ያሏት አገር ናት ።

"አሁን ላይ የጋራ የአብሮነት እሴቶቹን በማላላትና ትውልዱን በዘርና በሃይማኖት በማቃቃር እርስ በርስ እንዲጠራጠር የሚያደርጉ ጽንፈኞች እዚህም እዚያም እየታዩ በመምጣታቸው ዜጎች በጋራ ልንመክታቸው ይገባል" ብለዋል ።

የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎቹ አክለው  ትውልዱ የቆየውን ባህልና የአብሮነት እሴቶቹን በመጠቀም በየጊዜው የሚገጥሙ ችግሮችን መመከትና ለመጪው ትውልድ የምትመች አገር መፍጠር እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ መሐመድ አብዱራህማን እንዳሉት "የሰው ልጅ በፈጣሪ ፊት እኩል ነው"፡፡

"በቅዱስ ቁርዓን አስተምህሮም "ሰውን በዘርና በሃይማኖት ማበላለጥ፣ መጥላትና ማፈናቀል ብሎም ከጥፋተኞች ጋር ማበርም የተከለከለ ነው" ብለዋል።

ሼህ መሐመድ እንዳሉት  ዜጎች ለጎረቤታቸው ችግር ደራሽ፤  ለተራበ አጉራሽ ሆነውና ከግጭትና ጥላቻ አመለካከት በፀዳ አብሮነት የሚኖር ትውልድ መገንባት ይጠበቅብናል ይላሉ፡፡

በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ወንጌል ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ፍቅረዮሐንስ ተሾመ  በበኩላቸው በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ "ፈጣሪ ሰው በመንደር፣ በዘር፣ በሃይማኖት ሳትከፋፈሉ እኔ እንደምወዳችሁ ተዋደዱ" ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡

የጥንት አንድነትና አብሮነት እሴታችን እንዳይጠፋ "የተጣላን ማስታረቅ፤ የተቸገረን መርዳት፣ የተሳሳተን ማስተማር እንዲሁም ይቅር መባባል" ቤተ ክርስቲያን ዘወትር የምታስተምረው መልካምነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"መሰል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችንን በመጠቀም ከጨለማ ጥላቻ ብርሃን ወደ ሆነው መዋደድ መመለስና አንድነታችንንና አብሮነታችንን አጠናክረን መቀጠል ይገባል" ሲሉ መምህር ፍቅረዮሐንስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌና የምዕራብ ሀረርጌ ዞን የሰላም አምባሳደር አቶ አህመድ አልዪ በሰጡት አስተያየት "እርስ በርስ መናናቅና መገዳደል የኢትዮጵያዊነት መገለጫ አይደለም" ብለዋል፡፡  

"ኢኮኖሚውን በማድቀቅ፣ የኑሮ ውድነት በማናር ችግር እየፈጠሩ ያሉ ሀገርን በመሸጥ የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋቸዋል" ያሉት አቶ አህመድ፤ "ባልሆነ አፈታሪክ አእምሮውን መርዞ ሀገር ለመሸጥ እየተንደረደረ ያለውን ዜጋ የመመለስ ጉዳይ የሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው "ብለዋል፡፡

"የሀገር ሽማግሌዎች ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ትውልዱን ከጥፋት የማዳን ድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል" ያሉት የሰላም አምባሳደሩ፤ የቆየው የአብሮነት እሴቶቻችንን በትክክል መተግበር  ደግሞ ለችግሮቻችን ፍቱን መድሃኒት ነው" ሲሉ አመልክተዋል።

"ህዝቦች ሳይጠላሉና ሳይከፋፈሉ እንደ ጥንቱ አባቶቻችንና እናቶቻችን የጋራ እሴቶቻቸውን ጠብቀው ቢኖሩ ሀገራዊ ሰላማችን አስተማማኝ ይሆናል ያሉት ደግሞ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት የሰላምና እሴት ግንባታ ኃላፊ አቶ አወል አህመድ ናቸው፡፡

"የተጣላን አስታርቆ፤ ለተቸገረ ረድቶ፤ እንግዳ ተቀብሎ በአብሮነት ተከባብሮ የሚኖርበትን ጊዜ መመለስ በአሁኑ ግዜ የሚገጥመውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመመከት ወሳኝ ነው" ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም