በአፋር ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ሰመራ ፤ሚያዚያ 28/2014 (ኢዜአ) በዘንድሮ የበጀት ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የተገኘው ገቢ በዘጠኝ ወሩ ለመሰብሰብ  ከታቀደው  1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር   ውስጥ  መሆኑን የቢሮው ሃላፊ አቶ መሐመድ ሀሰን ገልጸዋል።

ሃላፊው እንዳሉት፤ ገቢው   ቀጥተኛ፣ ቀጥተኛ ካልሆኑ የግብር ታክሶችና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች  ሲሆን፤ አፈጻጸሙ  የእቅዱን  82 በመቶው የሸፈነ ነው።  

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ304 ሚሊዮን ብር  እድገት እንዳለው ገልጸዋል።

የህወሃት ሽብር ቡድኑ በክልሉ የፈጸመው ወረራና የንግዱ ማህበረሰብ ገቢን በቅንነት አሳውቆ በወቅቱ የመክፈል ልምድ አለመጎልበት ለእቅዱ ሙሉ ለሙሉ አለመሳካት ሃላፊው በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል።

በገቢ አሰባሰቡ ላይ የታዩ ክፍተቶችን በመለየት በተካሄደው እንቅስቃሴ ባለፉት ወራት ዘጠኝ ወራት ግብርን ያለአግባብ ለመሰወር በሞከሩ 26 ድርጅቶች ላይ የገንዘብ ቅጣትና ማስጠንቀቂያ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።

በቀሪ ወራት የበጀት ዓመቱን እቅድ ለማሳካት  በየደረጃው የሚገኘው አመራር ለገቢ አሰባሰቡ ትኩረት ሰጥቶ የንግድ ማህበረሰብ ግንዛቤና ደረሰኝ የመስጠት ልምዱ ለማዳበር  የንቅናቄ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።


በሎግያ ከተማ በአልባሳት ንግድ ስራ   የተሰማሩት አቶ ተማም አብደላ በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት የሚያከናውነው የልማት ስራዎች  በሚከፍለው ግብር መሆኑን እንደሚረዱ ተናግረዋል።
በንግድ ስራቸው ከሚያገኙት ትርፍ ላይ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ በመከፈል የዜግነት ግዴታቸውን መወጣታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ሌላው በከተማው በሸቀጣ-ሸቀጥ ንግድ ላይ የተሰማሩት አብዱኑር መሀመድ፤  በተሰማራበት  ስራ የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል ግዴታቸውን እየተወጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ  በክልሉ ለመሰብሰብ የታቀደው የገቢ ግብር ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ  መሆኑ ተመልክቷል።

በበአፋር ክልል በተለያዩ የንግድ ስራ መስክ የተሰማሩ ከ15ሺህ  በላይ   ግብር ከፋይ ነጋዴዎች እንደሚገኙ የገቢዎች ቢሮ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም