መገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ የሚያደርሱበት ፖሊሲ ተቀርጾ እየተተገበረ ነው-ባለስልጣኑ

ባሀር ዳር ሚያዝያ 28/2014(ኢዜአ) በአገሪቱ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ የሚያደርሱበት ፖሊሲ ተቀርጾ እየተተገበረ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አስታወቀ።

"ለውጥ፣ተግዳሮትና ቀጣይነት ያለው የሚዲያ ሪፎርም በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል መገናኛ ብዙኃንና  ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ኮንፈረንስ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በኮንፈረንሱ ላይ እንደተናገሩት የባለድርሻ አካላትን ግብዓቶች በማካተት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው የመገናኛ ብዙሀን ፖሊሲ ወደ ትግበራ ገብቷል።

"ፖሊሲው የጸደቀው በሀገሪቱ ከመጣው ለውጥ ጋር ተያይዞ መንግሥት ጠንካራ መገናኛ ብዙሀን  ለመፍጠር በገባው ቃል መሰረት ነው" ብለዋል።

ፖሊሲው በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙኃን በአሰራራቸው፣ በአደረጃጀታቸውና በሚያቀርቡት ይዘት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት መሰረት እንደሚጥል አቶ ግዛው አመልክተዋል።

በተጨማሪም መገናኛ ብዙኃን በዓይነትም ሆነ በቁጥር እንዲስፋፉ፣ አቅማቸው እንዲገነባና ለህዝቡ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ እንዲያደርሱ ዓይነተኛ መሳሪያ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አየለ አዲሱ በበኩላቸው በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን መረጃን በወቅቱ፣ በጥራትና በፍጥነት በማድረስ በኩል ክፍተቶች እንደሚታዩባቸው ገልጸዋል።

"በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን እንደ ባህል ተደርጎ የተወሰደው መረጃን የመንፈግ ዝንባሌ በማረም በየሰዓቱ የሚሰራጩ አፍራሽና ሀሰተኛ መረጃዎችን ማጋለጥ ያስፈልጋል" ብለዋል።

መገናኛ ብዙኃን  በሃይማኖት፣ በጎሳ፣ በብሄርና በቡድን የሚገለጽ ዋልታ ረገጥነት ችግር እንደሚስተዋልባቸው የተናገሩት አቶ አየለ፣ "በዚህም የሃሳብ ብዝሃነት፣ ሰብአዊነትና ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚደረገው ትግል ችግር ውስጥ ወድቋል" ብለዋል።

ከችግሮቹ መላቀቅ የሚቻለው በመቀራረብና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ውይይት በማድረግ ጭምር መሆኑን አመልክተዋል።

አይ.ኤም.ኤስ ፎጆ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ሚስ ሶፊ ባየረነስ ማህበራቸው በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንን ለማሻሻል በሚደረገው እንቅስቃሴ  ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን በማጠናከር፣ በአቅም ግንባታ እንዲሁም  ራሳቸውን በራሳቸው የሚቆጣጠሩበትን አካሄድ እንዲከተሉ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

"በተጨማሪም በኢትዮጵያ ማህበረሰቡን የሚያገለግል ብቃት ያለው መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኝነት እንዲስፋፋ የተጠናከረ ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል።

የአማራ ክልል የጋዜጠኞች ማህበርና አጋር አካላት ትብብር የተዘጋጀውና ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ የዩኒቨርሲቲዎች የዘርፉ ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም  አጋር አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም