ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ለመጥፋት በተቃረቡ ሀገር በቀል ዛፎች ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት የዘርፉ ምሁራን

አዳማ ሚያዝያ 28/2014 (ኢዜአ) በሀገራዊ የአሩንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለመጥፋት በተቃረቡ ሀገር በቀል ዛፎች ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት የዘርፉ ምሁራን አመለከቱ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት ምሁራን  መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዴቢሳ ለሜሳ እንደገለጹት በሀገራችን የሀገር በቀል ዝርያ ላላቸው እጽዋት  ጨምሮ ዛፎች  በየጊዜው በሚደርሰው ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ጫና እየተመናመኑ ነው።

"ሀገር በቀል እጽዋትና ዛፎች  በተለይ ስነ ምህዳርን ለመጠበቅ ቁልፍ ሚና ላለው የደን ልማት የጎላ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል"።

ይሁንና በሀገራችን ብቻ የሚገኙ የሃበሻ ፅድ፣ ኮሶ፣ ዝግባና ሌሎች ዛፎችና የእፀዋት ዝሪያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚደርስባቸው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ጫና እየተጎዱ በመሆኑ በሀገራችን የደን ሀብቱ እንዲመናመንና በረሃማነት እንዲስፋፋ ምክንያት እየሆኑ መሆኑን ፕሮፌሰር ዴቢሳ ተናግራል።

በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለው  የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር  በብዘሃ ህይወት ሀብትን ከመጠበቅ   በተለይ ሀገር በቀል ዛፎችን በማልማት ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ ሊካሄድ እንደሞገባ አመልክተዋል ።

በአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በምርትና ምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየደረሰ መሆኑን ጠቁመው "እየተከናወነ ያለው የአሩንጓዴ አሻራ መርሀግብር  ለደን ልማት ወሳኝ ሚና ባላቸው ሀገር በቀል ዛፎች ላይ ትኩረት በማድረግ መሰራት አለበት" ብለዋል።

ሀብቱን ለመታደግና በዘላቂነት ለማልማት የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብርን ጨምሮ  በአካባቢ ጥበቃና የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በአግባቡ በሳይንሳዊ መንገድ ማከናወን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

"የዘርፉን ፖሊስና ስትራቴጂ ከመፈተሽ  ጀምሮ በደን ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃና በስርዓተ ምህዳር ስራ ውስጥ ሀገር በቀል የዛፍና እፀዋት ዝርያዎች ላይ ትኩረት ያደረገ  የችግኝ ተካለ ስራ ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራን ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብዘሃ ህይወት እንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ ናቸው።

በመጪው ከረምት የሚከናወነው የአሩንጓዴ አሻራ ግብር  የጠፉና ለመጥፋት የተቃረቡ ሀገር በቀል የሆኑ ለደን ልማት የጎላ ጠቀሜታ ያላቸውን የዛፍ ዝሪያዎች በመለየት ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ በተከላው ወቅት ትኩረት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለጥፋት የተጋለጡ ብርቅዬ ለሆኑ  የሀገር በቀል ዛፎችና እጽዋት ቅድሚያ በመስጠት በመርሀ ግብሩ እንዲተከሉ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በግብርና ሚኒስትር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዳይሬክተር  አቶ ተፈራ ታደሰ ናቸው።

በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለደን ልማት ወሳኝ ሚና ላላቸው የዛፍና እፀዋት ዝርያዎች ልማት  ትኩረት መሰጠቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም