ቀጥታ፡

ኢሰማኮ ከኤርትራ አቻው ጋር ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ ጳግሜ 2/2010 የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌፌሬሽን /ኢሰማኮ/ ከኤርትራ አቻው ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ውይይት አካሄደ። በሁለቱ አገራት መካከል በድንበር ግጭት ምክንያት ላለፉት ሃያ ዓመት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ሁለቱ መንግስታት ባደረጉት ጥረት እንደገና ማደስ ተችሏል። ይህን ተከትሎ የተለያዩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከርም  በኢሰማኮ  ፕሬዝዳንት  አቶ ካሳሁን ፎሎ የተመራ የልዑካን ቡድን ከነሐሴ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ. ም በአስመራ ቆይታ አድርጓል። በቆይታውም ከኤርትራ አቻው ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመፍጠር ውይይት ያደረገ ሲሆን ሁለቱ  ማህበራት ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባሻገር የአገራት ሰላምና መቀራረብ ስር እንዲሰድ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። እንዲሁም በሁለቱ አገራት መካከል በጋራ ለመስራት የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሰራተኛ ውክልና ያለውና ከሰራተኛ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ስራዎችን የሚሰራ ተቋም ለማቋቋም  ውይይት አድርገዋል። የልዑካን ቡድኑ በአስመራ ከተማና በምጽዋ ወደብ የተሰሩ የተለያዩ የልማት ስራዎችን የጎበኘ ሲሆን የኤርትራ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አባላትን ሙያዊ አቅም ለማጎልበት እየሰራ ያለው ስራም አመርቂ መሆኑን ለመገንዘብ ችሏል። የኤርትራ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አመራር አባላት ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጥሪ እንደተደረገላቸው ኮንፌዴሬሽኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አመልክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም