ቀጥታ፡

የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ለውጡን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለጹ

መተማ ጳጉሜ 2/2010  በሀገሪቱ የተጀመረውን ምቹ የፖለቲካ መስመርና የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል  ከመንግስትና ከህዝቡ ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ገለጹ፡፡ ከአባላቱ መካከል የምዕራብ ጎንደር ዞን ተወላጆች ወደ ትውልድ  ቀያቸው ሲመለሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በአቀባበል ስነሰርዓቱ ወቅት አባላቱ ለኢዜአ እንዳሉት  በአካባቢያቸው ስርዓት አልበኝነትንና ፀረ-ህዝብ የሆነ እንቅስቃሴን ለመታገል ዝግጁ ናቸው፡፡ ይናገር ተሰማ ከአባላቱ መካከል አንዱ ሲሆን  በሀገሪቱ ያለውን ለውጥ ዳር ለማድረስ፣ የግለሰቦች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማስከበር እንደሚሰራ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተሻለች ኢትዮጵያ ለመገንባትና በማንም የማይቀለበስ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲኖር ከመንግስትና ህዝብ ጋር በመሆን የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡ " የትግል ሜዳውን ቀየርን እንጂ ትግሉን አላቆምንም" ያለው አባሉ ለዚህ ለውጥና ደረጃ ላበቁት መሪዎች ያለውን ክብርና ምስጋናውን ገልጿል፡፡ ሌላው አባል  ግርማይ ደባሽ በበኩሉ አሁን ካለው የለውጥ ኃይል ጋር ተቀራርቦ በመስራት ፍትህ እንዳይጓደልና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን  የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡ በሰላማዊ ትግል ለኢትዮጵያ አንድነት መጠናከር ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆኑም  ጠቁሟል፡፡ አሁን ባለው የህዝብ ነጻነት መደሰቱን የገለጸው ደግሞ ሌላው የድርጅቱ አባል ዮሐንስ  ታረቀኝ የአካባቢው አስተዳደር ደግፏቸውና አቅርቧቸው እንዲያሰሯቸው ጠይቀዋል፡፡ በአቀባበል ስነስርዓቱ ወቅት የተገኙት የገንዳውሃ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ አቶ ሞላ ሁሴን ከትግል የተመለሱ ወጣቶችን ከከተማው ማህበረሰብ ጋር በመሆን አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡ "እንደ ተፎካካሪ የፖለቲካ ደርጅት አባል ልዩነታቸውን በማክበር አንድ በሚያደርጋቸው ነገር ተቀራርበን እንሰራለን" ብለዋል፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ካቢኔ አባላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ወቅት ተገኝተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም