ብሔራዊ ቡድኑ በሁለቱም ጾታ ምስራቅ አፍሪካን ወክለው በአፍሪካ ሻምፒዮና ለመወዳደር የሚያችላቸውን ውጤት አስመዘገቡ - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ቡድኑ በሁለቱም ጾታ ምስራቅ አፍሪካን ወክለው በአፍሪካ ሻምፒዮና ለመወዳደር የሚያችላቸውን ውጤት አስመዘገቡ
ሚያዚያ 28/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን በቡድን ጨዋታ በሁለቱም ጾታ ተጋጣሚያቸውን በማሸነፍ ምስራቅ አፍሪካን ወክለው በአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ለመወዳደር የሚያችላቸውን ውጤት አስመዘገቡ።
ዘጠኝ አገራት እየተሳተፉበት የሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ከተማ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ሻምፒዮና በቡድን ጨዋታ በሁለቱም ጾታ ለፍጻሜ ያለፉ አገራት ተለይተው ታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን በቡድን ጨዋታ የሴቶች ጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚቸውን ሲሼልስ በማሸነፍ ለፍጻሜ ማለፍ ችለዋል።
በወንዶች ደግሞ ዩጋንዳን ብሔራዊ ቡድን በመርታት ነው ቡድኑ ለፍጻሜ ያለፈው።
በዚህ ሻምፒዮና ለፍጻሜ የሚያልፉ አገራት ምስራቅ አፍሪካን ወክለው 2022 በአልጀሪያ በሚደረገው የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ተካፋይ ይሆናሉ።
በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን በሁለቱም ጾታ ምስራቅ አፍሪካን ወክለው በአፍሪካ በአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና የሚሳተፉ ይሆናል።
ሌላኛው በቡድን የጠረጴዛ ቴኒስ ጨዋታ በወንድም በሴትም ምስራቅ አፍሪካን የሚወክሉት የሞሪሺየስ ብሔራዊ ቡድን ናቸው።
ምስራቅ አፍሪካን ወክለው በአፍሪካ ተሳታፊነታቸውን ያረጋገጡት የኢትዮጵያና የሞሪሽየስ ብሔራዊ ቡድን የፍጻሜ ጨዋታ እሁድ የሚደረግ ይሆናል።
በነጠላ ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ደግሞ ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ የሚደረጉ ሲሆን በዚህም ውድድር ለፍጻሜ የሚያልፉ አገራት በአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ተሳታፊ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እየተካሄደ የሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ሚያዚያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ይሆናል።