የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ከጣዝማ የውስጥ ደዌና ቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል ጋር በትብብር ለመሥራት ተስማማ - ኢዜአ አማርኛ
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ከጣዝማ የውስጥ ደዌና ቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል ጋር በትብብር ለመሥራት ተስማማ
ሚያዝያ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ከጣዝማ የውስጥ ደዌና ቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል ጋር በልብ ቀዶ ሕክምና ላይ በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ።
ማዕከሉ ከ300 ሺህ ዶላር ዋጋ ያለው የልብ ቀዶ ሕክምና ማሽንም ለሆስፒታሉ አስረክቧል።
ሥምምነቱን የኮሌጁ ፕሮቮስት ዶክተር ወንድማገኝ ገዛኸኝና የማዕከሉ ቦርድ ሊቀ-መንበር ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ፈርመውታል።
የጣዝማ ውስጥ ደዌና ቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል በስውዲሽ መንግሥትና በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀስ በተለይም በልብ ቀዶ ሕክምና የታወቀና የአዲስ ልብ ህክምና ክሊኒክ እህት ኩባንያ መሆኑ ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኮሌጁ ከማዕከሉ ጋር በልብ ቀዶ ህክምና መሥራቱ መንግሥት የግሉን ጤና ተቋማት ተሳትፎ ለማሳደግ ከቀረፀው ፍኖተ ካርታ አንዱ አካል ነው ብለዋል።
ሥምምነቱ ኮሌጁ የአገልግሎት አድማሱን እንዲያሰፋ፣ በልብ ቀዶ ሕክምና በቂ የሰው ኃይል ለማፍራትና በህክምና እጦት የሚንገላቱ ወገኖችን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
የጤና ተቋማት አገልግሎት ለማስፋፋት የዕውቀት ሽግግር ለመፍጠር የጎላ ሚና እንደሚኖር ገልፀዋል።
ጤና ሚኒስቴር የመግባቢያ ሥምምነቱ ገቢራዊ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋገግጠዋል።
የማዕከሉ የቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በበኩላቸው የግልና የመንግሥት ጤና ተቋማት ለብቻ ከመቆም በትብብር ቢሰሩ የዕውቀት ሽግግር በማድረግ ባለሙያዎችን ለማፍራት ብሎም ህሙማኑን ለመታደግ ያስችላል ነው ያሉት።
ከሆስፒታሉ ጋር በትብብር ለመሥራት ሥምምነት ማድረጉም የጣዝማ ሕልም እንደተፈታ እንቆጥረዋለን ነው ያሉት።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ፕሮቮስት ዶክተር ወንድማገኝ ገዛኸኝ በበኩላቸው የሥምምነቱ ዋና ዓላማ ቀጣይነት ያለው የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠትና በዘርፉ ባለሙያዎች በቂ ሥልጠና እንዲያገኙ አጋርነት መፍጠር እንደሆነ ገልፀዋል።
የመንግሥትና የግል ተቋማት በትብብር ከሰሩ ውጤታማና ቀጣይነት ያለው የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ ዕድል እንዳለው አብራርተዋል።