በሀገራዊ ምክክሩ ከራስ ጥቅም ይልቅ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በማስቀደም ሊሆን ይገባል -አቶ አባተ ኪሾ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክሩ ከራስ ጥቅም ይልቅ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በማስቀደም ሊሆን ይገባል -አቶ አባተ ኪሾ
ሀዋሳ ፤ ሚያዚያ 28/2014 (ኢዜአ) በሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ከራስ ጥቅም ይልቅ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በማስቀደም ሊሆን እንደሚገባ የቀድሞው የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አባተ ኪሾ ተናገሩ።
ባህላዊ እሴቶችን መተግባር ከተቻለ ዘላቂ ሃገራዊ ሰላም ማምጣት እንደሚቻል ነው ያመለከቱት።
አቶ አባተ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሀገር በቀል ዕውቀትን መጠቀም፣ ህዝቡንም ካለምንም ልዩነት ማቀራረብና ለውይይት ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
በተለይ እንደ ፊቼ ጫምበላላ ያሉ የባህላዊ እርቅ ስርዓት ትሩፋቶችን ሥርዓትና ስልት መከተል ችግርን በመነጋገር ለመፍታትና ለሃገር ሰላም ለዘላቂ ሠላምና እንድነት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህም ለሃገራዊ ምክክር ስራ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸው ህዝቡም መድረኮቹን ለመጠቀም ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበትና በጥያቄዎቹ ላይ መተማመን መፍጠር ይገባዋል ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ ዜጎች ከራስ ጥቅም ይልቅ ሀገራዊ አንድነትን በማስቀደም ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በተለይ የሀገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርሻቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው ብለዋል።
''ህዝቡ ከባህሉና እምነቱ ውጪ አይደለም'' ያሉት አቶ አባተ፤ ከውይይት ውጭ በአፈሙዝ የሚፈታ ችግር ስሌለለ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ሥራ ማገዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ችግሮቻችን በራስ መፍታት የሚያስችል ሃገር በቀል ዕውቀት ባለቤት መሆናችንን በማወቅም ባህላዊ ሃብቶቻችንን ለሃገር ሰላም ማዋል ይገባናል ብለዋል፡፡
ለይቅርታ ትልቅ ስፍራ ያላቸውና ቁጭ ብሎ መነጋገርን የሚፈቅዱ ባህላዊ እሴቶች እያሉን እርስ በርስ መጣላትን ማቆም ይገባልም ብለዋል አቶ አባተ።
ሳይማሩ የአብሮነትን እሴት ያቆዩ አባቶችን ልምድ በትምህርት መደገፍ እንደሚገባና ነገሮችን በትዕግሥት ማለፍ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
የሲዳማን የ"አፊኒ" ባህል በችግሮች ላይ ተወያይቶ መፍትሄ እንደሚያመላክት ለአብነት ያቀረቡት አቶ አባተ፤በየአካባቢው ያሉትን ባህላዊ እሴቶች መተግበር ከተቻለ የምንመኘውን ሃገራዊ ሰላም ማምጣት እንችላለን ብለዋል።