ቀጥታ፡

በአገሪቱ አብዛኛው አካባቢዎች የሚጠበቀውን የግንቦት ወር ዝናብ በአግባቡ ለመጠቀም ዝግጅት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2014 /ኢዜአ/  በአገሪቱ አብዛኛው አካባቢዎች የሚጠበቀውን የግንቦት ወር ዝናብ በአግባቡ ለመጠቀምና ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ የግንቦት ወር ዝናብ ሰጪ የሜትሮሎጂ ገጽታዎች በተለያዩ የአገሪቱ ሥፍራዎች ላይ አንጻራዊ ጥንካሬያቸውን ይዘው እንደሚቀጥሉ የትንበያ መረጃዎቹን ይጠቁማሉ ብሏል።

ይህንም ተከትሎ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ እንደሚኖር ትንበያ አስቀምጧል።

በደቡብ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና  በጋምቤላ አካባቢ ጥቂት ሥፍራዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ የማስከተል አቅም ያለው ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችልም ተጠቁሟል።

በግንቦት ወር ከምስራቅ ሃረርጌ ምስራቅ ዞኖች በስተቀር በሁሉም የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ላይ፣ በቤንሼንጉል፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ክልል፣ በሲዳማ ክልል በሁሉም ዞኖች  እንዲሁም በአማራ ክልል በአዊ፣ በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች ላይ ከመደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል።

አልፎ አልፎ ከሚፈጠሩ የደመና ከምችቶች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃው ያመለክተል።

በተጨማሪ በጎንደር ሁሉም ዞኖች በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣  ከአፋር ክልል፣ በምስራቅ ሀረርጌ፣ በምስራቅ ባሌ፣ ከሱማሌ ክልል በዳዋ፣ በሊበንና አፍዴራ ዞኖች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል።

በተቀሩት የአገሪቱ አከባቢዎች ደረቃማ ሆነው እንደሚሰነብቱ የአየር ትንበያው መረጃ አመላክቷል።

ከቀላል እስከ ከባድ የሚጠበቀው የዝናብ መጠን በአብኛዛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ለረጅም ጊዜ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውኃ ፍላጎት መሻሻል ትልቅ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

የሚገኘውን ውኃ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የተለያዩ የውኃ ማቆያ ዘዴዎችን አጠናክሮ በመጠቀል ዝናበ አጠር አካባቢዎች ለሚያጋጥማቸው የእርጥበት እጥረት ለማቃለል እንደሚረዳ ተገልጿል።

ከባድ ዝናብ በሚከሰትባቸው የአገሪቱ አከባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያጋጥም ስለሚችል ሰብሎች እንዳይጎዱ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

በተጨማሪም የእርጥበት መብዛት ጋር የጸረ-ሰብል ተባይና የአረም መከሰት ሊኖረ ሰለሚችል ለዚህም ጥንቃቀቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተጠቅሷል።  

በሌላ በኩል ከክረምት እርጥበት መጠናከር ጋር ተያይዞ በደቡብ ምዕራብና በምዕራቡ የአገሪቱ የውኃ አካሎች ላይ የእርጥበት መጠኑ እንደሚጨምርም ተመላክቷል።

ይህንንም የእርጥበት መጠን ጥቅም ላይ ለማዋልና የሚያስከትለውን አሉታዊ ጎን ለመከላከል ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቲ በመግለጫው ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም