ቀጥታ፡

የአርበኞች የድል በዓል ኢሉባቦር ዞን ሳምቤ ተራራ በተለያዩ ሁነቶች ታስቧል

ጎሬ፣ ሚያዝያ 28/2014 (ኢዜአ) የፋሺስት ኢጣሊያን ወራሪ ጦር ድል የተመታበትና ኢትዮጵያውያን አርበኞች የመጨረሻውን ነፃነት የተቀዳጁበት የአርበኞች የድል በዓል ቀን ኢሉባቦር ዞን ጎሬ ከተማ ሳምቤ ተራራ ታስቦ ዋለ።

የኢሉባቦሩ ሳምቤ ተራራ በታሪክ ቅኝ ላለመገዛታችን ትልቁን ድርሻ የተወጡት የአባቶቻችን ፋሽስት ኢጣሊያንን ድል ከነሱባቸው አውደ ውጊያዎች አንዱ ነው።

የኢጣሊያን ጦር አዲስ አበባን መቆጣጠሩን ተከትሎ በወቅቱ በነበረው አስተዳደራዊ መዋቅር ስያሜ የኢሉ ባቦር ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ የነበረችው ጎሬ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ለማገልገል ደርሳ እንደ ነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

የሀገራቸው ሉዓላዊነት በፋሺስት ኢጣሊያን ጦር መደፈሩ የእግር እሳት የሆነባቸው ጀግኖች የኢትዮጵያዊያን አርበኞች ጎሬ ላይ ተሰባስበው ወራሪውን ኃይል በሀገር ፍቅር ወኔ ለመፋለም አንድነታቸውን አጠናከሩ።

የፋሺስት ኢጣሊያን ጦር በደረሰበት የጀግኖች አርበኞችን ምት መቋቋም ተስኖት ሳለ የኢትዮጵያዊያን ጎሬ ላይ እንደገና መሰባሰብና መጠናከር ተበሳጭቶ ጎሬንም ለመውረር ተንቀሳቀሰ።

ኑሯቸውን በዱር በገደሉ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን አርበኞችና የአካባቢው አርሶ አደሮች በሳምቤ ተራራ ላይ  በፈጸሙት አኩሪ የጀግንነት ተጋድሎ የኢትዮጵያን ነፃነት እንዳወጁም ድርሳናቱ ይነገራሉ።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማንና የክልሉ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት  81ኛው የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የድል በዓል ቀን መታሰቢያ በኢሉባቦሩ ሳምቤ ተራራ ተከብሯል።

ጦርነቱ በተካሄደበት ከጎሬ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኢኖስ ሳምቤ ቀበሌ በሚገኘውና ታሪካዊው የሳምቤ ተራራና የአካባቢው መስዕብ ስፍራዎችም ተጎብኝተዋል።

ወይዘሮ ሰዓዳ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት የቀደምት አባቶቻችንን የድል ታሪኮችና ስፍራዎችን ከመዘከር ጎን ለጎን ዛሬ እያጋጠሙን ያሉ ውስብስብ ችግሮን በጋራ በማሸነፍ እኛም ሌሎች የድል ታሪኮችን ማስመዝገብ መቻል አለብን ብለዋል።

ሰላምን በማስጠበቅ፣ የአባቶችን ድል በማስቀጠል ድህነትን በማሸነፍና ብልፅግናን በማረጋገጥ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ከእኛ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ማወቅ ይጠበቅብናል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በተፈጥሮ የበለፀገ አካባቢ እየኖርን በድህነት መማቀቅን ታሪክ ማድረግ ትልቁ ከእኛ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን መዘንጋት የለብንም ሲሉም በአፅኖት ተናግረዋል።

በመሆኑም ለሁሉም ሀገራዊ ድልና ስኬት ቁልፍ መሳሪያ የሆነውን አንድነታችን እና አብሮነታችንን መጠበቅና ከምንጊዜውም ማጠናከር ይገባናል ሲሉም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያውያን አርበኞች የፋሺስት ኢጣሊያን ጦር እንቅስቃሴና የሎጂስቲክ አቅርቦት ለመግታት ቀበር ወንዝ ላይ የነበረውን ድልድይ በመስበር ሳምቤ ተራራን መቀበሪያውና መማረኪያ እንዳደረጉት የኢሉባቦር ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የታሪክ ተመራማሪ አቶ ተመስገን ኮርጄ ገለጸዋል።

በዚሁ በ1933 ዓ.ም በተደረገው እልህ አስጨራሽ የሳምቤ ጦርነት 1ሺህ 558 የወራሪው ፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች ሲደመሰሱ፤ ከ1 ሺህ 800 በላይ ደግሞ መማረካቸውን ተመራማሪው ተናግረዋል።

እንዲሁም ከ20 ሺህ በላይ የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎች፣ ከ100 በላይ መትረየሶችና 50 ያህል መድፎችና የአየር መቃወሚያዎች መማረካቸውን ተመራማሪው አስረድተዋል።

ከወራሪው ፋሺስት ኢጣሊያ ጦር የተማረኩት የጦር መሳሪያዎች ወደ አዲስ አበባ ተወስደው ለሀገሪቱ ፀጥታ ኃይሎች ማጠናከሪያ እንዲውሉ መሰጠታቸውን አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን አርበኞች በሀገር ፍቅር የጀግንነት ተጋድሎ ዓድዋ ላይ ጣሊያንን ድል በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር የነጭን የበላይነት አስተሳሰብን ማሸነፍ እንደሚችል ለዓለም ሕዝብ አስታውቀዋል።

በዓደዋው ጦርነት በተጎነጨው የሽንፈት ፅዋ የተበሳጨው ፋሽስት ጣሊያን ሽንፈቱን ለመበቀል ከ40 ዓመት ዝግጅት በኋላ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቆ ዳግም ኢትዮጵያን ለመውረር መጥቶ በኢትዮጵያውያን አርበኞች ድል ተመቶ የሽንፈትና የውርደት ካባ ተከናንቧል።

የኢሉባቦሩ ሳምቤ ተራራ ላይ በተከበረው 81ኛው የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የድል ቀን መታሰቢያ በዓል ላይ ከጋምቤላ ክልል የመጡ ተጋባዥ እንግዶች መሳተፋቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም