ኢትዮጵያ ጊኒ ዎርምን ለማጥፋት ለጀመረችው ስራ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

137

ጋምቤላ፤ ሚያዚያ 27/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የጊኒ ዎርም በሽታን ለማጥፋት ለጀመረችው ስራ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

በጋምቤላ ክልል የጊኒ ወርም በሽታን ለማጥፋት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በመስክና በመድረክ የፌዴራል ፣የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና አጋር አካላት በተገኙበት ተገምግሟል ።

በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ተጠሪ ዶክተር ዲላሚኒ ኖነሃላነሃል/ Dlamini Nonhlanhla/ በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የጊኒ ዎርም በሽታን ካላጠፉት ጥቂት  ሀገራት መከከል አንዷ ናት።

ጊኒ ዎርምን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር እስከ  2025 ከዓለም ለማጥፋት የተያዘውን ግብ እንዲሰካ ኢትዮጵያ የድርሻዋን ለመወጣት የጀመረቻቸው አበረታች ስራዎች አጠናክራ  እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

በተለይም በጋምቤላ ክልል የጊኒ ዎርም ስርጭት ባልተቋረጠባቸው ሁለት ወረዳዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻልን ጨምሮ በሽታውን ለማጥፋት የተጠናከረ አቅም በመፍጠር መስራት ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ባለፈው 2021 ዓመት የጊኒ ዎርም ስርጭትን ለመግታት የተከናወኑት ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ በመስክ ምልከታው ማረጋገጣቸውን ጠቁመው ፤ ለተገኘው ውጤት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በዘርፉ ለተጀመሩት ስራዎች ስኬታማነት አስፈላጊውን  ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ዶክትር ዲላሚኒ አስታውቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የጊኒ ዎርምን ለማጥፋት በርካታ ስራዎች በማከናወን አበረታች ውጤት ብታስመዘግብም በሽታው እስካሁን ካልጠፉባቸው ጥቂት ሀገራት ውስጥ መገኘቷ የሚያስቆጭ  ነው ብለዋል።

በሽታውን ከጋምቤላ ብሎም ከኢትዮጵያ ለማጥፋት  ከተቀመጠው ግብ በፊት ለማጥፋት የአጋር አካላትን ትብብርና ቅንጀትን በማጠናከር ሰፊ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በተለይም ለእቅዱ ስኬታማነት በየደረጃው ከሚገኙ የክልሉ የአመራር አካላት የላቀ ቁርጠኝነት እንደሚጠበቅ ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

የጊኒ ዎርም በሽታን ከክልሉ ብሎም ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የክልሉ መንግስት የተቻለውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርግ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌ ጆክ ናቸው።

ለተጀመሩት ስራዎች መሳካትም የፌዴራል መንግስትና ሌሎች የአጋር ድርጅቶች ድጋፍና ትብብር እንዳይለያቸው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል።

የጤና  ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከትናንት ጀምሮ የነበራቸውን መረሃ ግብር ዛሬ ማጠናቀቃቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።

የጊኒ ዎርም በሽታን በዓለም ያላጠፉ የአፍሪካ ሀገራት፤ ቻድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማሊ ፣ኢትዮጵያና አንጎላ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም