በክልሉ በአሸባሪው ህውሓት የሽብር የወደሙ ተቋማትንና መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እየሰራ ነው

71

ባህርዳር ሚያዚያ 27/2014 (ኢዜአ) የአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተቋማትንና የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ፕሮጀክት ነድፎ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ።

የንፋስ መውጫ ከተማን በአሸባሪው ህወሓት ከደረሰበት ውድመት ለመታደግ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ዛሬ  ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ መሰባሰቡ ተገልጿል።

በጽህፈት ቤቱ የፓለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሞላ መልካሙ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ፈጽሟል።

ንፁሃንን በመግደል፣ ሴቶችን በመድፈር፣ ንብረት በመዝረፍ፣ መሰረተ ልማቶችን በማውደም በክልሉ ላይ ግፍና ውድመት መፈጸሙን ተናግረዋል።

ወረራው ከተቀለብሰ ማግስት ጀምሮ በወረራ ስር የቆዩ አካባቢዎችን ወደ መልሶ ግንባታ መገባቱን ጠቅሰው፤ በመልሶ ግንባታ ላይ ካሉት ከተሞች መካከል የነፋስ መውጫ ከተማ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግስት የኢኮኖሚ ምንጭ የሆኑና የማህበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትንና መሰረተ ልማቶችን  መልሶ ለማቋቋም የፈንድ ጽህፈት ቤት በማቋቋም የሃብት ማሰባሰበ ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ከሰሜን ሸዋ እስከ ዋግ ኽምራና ሰሜን ጎንደር ድረስ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት በተቀናጀ መልኩ ሃብት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የመልሶ ማልማት ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን መላው የአማራና የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የልማት አጋሮች ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የጋይንት ነፋስ መውጫ ህዝብ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን ፋና ወጊ ድል ማስመዝገቡን ያስታወሱት ኃላፊው የወደሙ የመሰረተ ልማቶችን በመልሶ በመገንባት ሂደት የክልሉ መንግሥት ከነዋሪዎች ጋር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ በበኩላቸው የነፋስ መውጫ ከተማ አስተዳደር ከደቡብ ጎንደር ዞን መስተዳድር ጋር በመተባበር ቀድሞ ወደ መልሶ ግንባታ መግባት ችሏል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት የመልሶ ማቋቋም የአምስት ዓመት እቅድ ሳይጠብቅ የዞኑና የከተማ አስተዳደሩ አመራር የአካባቢውን ተወላጆች፣ ባለሃብቶችና የልማት አጋሮችን በማስተባበር ከተማዋን ለመቀየር መነሳቱ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልፀዋል።

"በጋይንት ግንባር በተካሄደው ጦርነት አሸባሪውን ቡድን በመደምሰስ ለሌሎች ግንባሮች አርዓያነት ያለው ድል የተመዘገበው ባሳየነው ትብብር ነው" ያሉት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ ናቸው።

"የመከላከያ፣ የልዩ ኃይልና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም መላ ህዝቡ በፈጸሙት ጀግንነትና መስዋዕትነት የጠላት ፕሮፓጋንዳን በመስበር የአሸናፊነት መንፈስን መላበስ ችለናል" ብለዋል።

በጦር ግንባር የጠላትን ቅስም መስበር ቢቻልም ወራሪው ኃይል ያደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለመልሶ ግንባታው የተዘጋጀው ቴሌቶን ሁሉንም አካል በማሳተፍ ነፋስ መውጫ ከተማን ለመገንባት የተያዘው ግብ እንዲሳካ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ለሚቀጥሉት አምስት ለተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚሁ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፤ ዛሬ በመጀመሪያው ቀን ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ  ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም