የአዲስ ዓመት በዓልን ተከትሎ ለሚፈጠረው የኃይል መቆራረጥ አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ኮሚቴ ተቋቋመ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ ዓመት በዓልን ተከትሎ ለሚፈጠረው የኃይል መቆራረጥ አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ኮሚቴ ተቋቋመ
አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2010 ከአዲስ ዓመት በዓል ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችለውን የኃይል መቆራረጥ በመከታተል አፋጣኝ መፍትሔ የሚሰጥ የጋራ ኮሚቴ መቋቋሙን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ገለጸ። በበዓሉ ከሚጠበቀው ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት አኳያ ሊያጋጥም የሚችለውን የኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለመከላከል በቂ ዝግጅት ማድረጉንም አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የበዓሉ ቀን ከመድረሱ በፊት ባሉት ጊዜያት ችግር ያስከትላሉ የተባሉ አካባቢዎችን በመለየት የተለያዩ የመልሶ ግንባታ፣ አቅም የማሳደግ፣ የጭነት ማመጣጠንና የቅድመ መከላከል ጥገና ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። በበዓሉ ቀን ሊፈጠር የሚችለውን የኃይል መቆራረጥ እክሎችን በመከታተል ለችግሩ አፋጣኝ የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ ይቻል ዘንድም አስፈላጊ የግብዓት አቅርቦት የተሟላ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል። ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የኃይል መጨናነቅ ሊከሰት ስለሚችል ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ አንዲያደርጉም አሳስቧል። በተለይም የድንጋይ ወፍጮ፣ የፕላስቲክ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የቆዳና የኬሚካል ፋብሪካዎች እንዲሁም ሌሎች የከፍተኛና መካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ከጳጉሜ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ እስከ መስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም ከንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ አማራጭ የኤሌትሪክ ሃይል እንዲጠቀሙ ጥሪውን አቅርቧል። ህብረተሰቡም የኤሌትሪክ ሃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት በተለይ ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 12 ሰዓት ቢጠቀም የተሻለ የአሌትሪክ ሃይል ማግኘት ስለሚችል የሚፈጠረውን የሃይል መጨናነቅ መቀነስ እንደሚያስችልም ተገልጿል። ኤሌትሪክ ሲቋረጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበሩ ማሽኖች፣ የማብሰያና ሌሎች በኤሌትሪክ የሚሰሩ እቃዎች ሶኬቶችንም መንቀል እንደሚያስፈልግም የኢትዮጵያ የኤሌትሪክ አገልግሎት አሳስቧል። ደንበኞች ከኤሌክትሪክ ጋር በተገናኘ ማንኛውንም ዓይነት መረጃ ሲፈልጉ ወዲያውኑ በአካል ወይም በአቅራቢያ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በመሄድ እና በአማራጭነት በአዲስ አበባ የሚገኙ ደንበኞች በነፃ ጥሪ 905 በመደወል ማሳወቅ እንደሚችሉም ገልጿል። በተጨማሪም ኤሌትሪክ በሚቋረጥበት ጊዜ ከስራ ሰዓት ውጪም ጥገና ለማከናወን የተቋሙ ባለሙያዎች ሊንቀሳቀሱ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግላቸው ተቋሙ ጥሪውን አቅርቧል።