ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ተጀመረ

ሚያዝያ 27/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በደማቅ ሁኔታ ተጀምሯል።

ዛሬ በተጀመረው የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኮሞሮስ፣ሩዋንዳ፣ሲሸልስ፣ ሶማሊያ ፣ጅቡቲ፣ ኡጋንዳ እና ሞሪሺየስ ተካፋይ አገሮች ናቸው።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ  የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጃገዊ ሮበርት፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዲሁም የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ብዛኔ ጨምሮ የተለያዩ አገራት እንግዶች ታድመዋል።

ውድድሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሚደረግ ሲሆን በሻምፒዮናውም ዘጠኝ አገራት ተሳታፊ ናቸው ።

ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚሁ ወቅት ስፖርት ለኢኮኖሚ እድገት ፣ለዲፕሎማሲ ግንኙነት መጠናከርና ለሰላም መስፈን ሚናው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መሰል ውድድሮች እርስ በእርስ በባህል ግንኙነት ለማጎለበትና ስፖርቱን ለማሳደግ እንደሚያግዙም እንዲሁ፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጃገዊ ሮበርት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ያደረገችውን ዝግጅት አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ ለውድድሩ ተሳታፊዎች፣ ስፖርተኞችና የልዑክ ቡድኑ አባላት ላደረገችው ደማቅ አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ አቅም ያላቸው የጠረጴዛ ቴንስ ስፖርተኞች እንዳሏት አስታውሰው፤ በቀጣይም መንግስት ስፖርቱን ለማጠናከር እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ብዛኔ፤ የጠረጴዛ ቴንስ በኢትዮጵያ ተወዳጅ ስፖርት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ስፖርቱ  በኢትዮጵያ በስፋት የተጀመረው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1948 መሆኑንና ኢትዮጵያ የዓለምና በምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ፌዴሬሽን አባል መሆኗን ለአብነት ገልጸዋል።

እንደዚህ አይነት ውድድሮች የወንድማማችነት ስሜትን ለማጎልበትና  ስፖርቱን ይበልጥ ለማነቃቃት እንደሚያግዙም ነው የተናገሩት።

በዘንድሮው ውድድር ከሌላው ጊዜ በተለየ በርካታ አገራት የተሳተፉበት መሆኑንም አቶ ተስፋዬ ጨምረው ገልጸዋል።

ውድድሩ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት መካሄዱ በቀጣይ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ልምድ እንደሚገኝበትም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ  የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት እንደሚያግዝም አክለዋል፡፡

የውድድሩ ተሳታፊ አገራት በወንዶችና ሴቶች ምድብ በእያንዳንዳቸው አምስት አትሌቶችን የሚያሳትፉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የውድድሩ አዘጋጅ በመሆኗ ተጨማሪ አትሌቶችን የማሳተፍ አድል አግኝታለች፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ 10 ወንድና 10 ሴት አትሌቶችን በውድድሩ የምታሳትፍ ይሆናል፡፡

በዚህ ውድድር አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች በ2022 አልጀሪያ በምታዘጋጀው የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና የሚካፈሉ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም