ቀጥታ፡

"ወጣቱ የሃገሩን አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ በጋራ ሊቆም ይገባል" - የጀግኖች አርበኞች ማህበር

ባህር ዳር ፤ ሚያዚያ 27/2014(ኢዜአ) ''ወጣቱ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹን ድል አድራጊነትን በመውረስ የሃገሩን አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ በጋራ ሊቆም ይገባል'' ሲል የአማራ ክልል ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አሳሰበ።

81ኛው የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የድል በዓል በባህር ዳር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።


የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ዳኝነት አያሌው በመረሃ-ግብሩ እንደገለጹት፤ ዛሬ ላይ ተከብራና ታፍራ የምትታወቀው ኢትዮጵያ የጀግኖች አባቶች መስዋትነትና ተጋድሎ ውጤት ናት።


በአድዋው ሽንፈት የተበሳጨው የኢጣሊያ  ወራሪ ከ40 ዓመታት በኋላ በከፍተኛ ዝግጅት ዳግም ለወረራ ቢመጣም ልክ የዛሬ 81 ዓመት በጀግኖች መስዋትነት አከርካሪው ተሰብሮ ተመልሷል ሲሉ አስታውሰዋል።


ወጣቱ ትውልድ ይህንን የአልደፈርም ወኔ አስጠብቆ ሃገሩን ለአደጋ ከሚያጋልጥ ከፋፋይ አጀንዳ ለመጠበቅ በጋራ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጀግኖች አባቶች መስዋትነት የከፈሉት ለሃገር ካላቸው የፀና ፍቅርና አንድነት እንደሆነ ጠቅሰው፤ በከፈሉት መስዋትነትም ያልተደፈረችና ነፃነቷ የተከበረች ኢትዮጵያን አስረክበውናል ብለዋል።

የዚህ ዘመን ትውልድም ሰላሟና አንድነቷ የጠበቀች ሃገርን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በአንድነትና በህብረት ሆኖ ከተደቀነባት አደጋ ሁሉ መጠበቅ ይገባዋል ሲሉ አመልክተዋል።


''የዛሬዋ ኢትዮጵያ ቀጣይ ህልውናዋ የሚረጋገጠው በወጣቱ ትውልድ ቆራጥነት ልክ ነው'' ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ፍታነገስት በዛብህ ናቸው።

የዛሬ 81 ዓመት መስዋትነት ከፍለው የሀገራቸውን ክብር ያስጠበቁት ዛሬ ጀግኖች በመባል የሚጠሩት የዛኔዎቹ ወጣቶች መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል ብለዋል።

ወጣቱ ትውልድ የነገ ሃገሩ የምትከበረውና የምትጠራው ዛሬ በሚሰራ መልካም ተግባር እንደሆነ አውቆ ለሃገሩ አንድነትና ሰላም ተባብሮ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

የዚህ ዘመን ትውልድ የሚጠበቅበት ሰርቶ ድህነትን ማሸነፍና ሃገሩን ወደ ብልፅግና ማሸጋገር በመሆኑ ለዚሁ መትጋት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በዓሉ በሙዚቃና በሌሎች ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን በበዓሉም የአባት አርበኞች፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ሌሎችም የከተማው ነዋሪዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም