በጋምቤላ ክልል የጊኒ ዎርም በሽታን ለማጥፋት እየተከናወኑ ያሉት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የጤና ሚኒስትሯ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የጊኒ ዎርም በሽታን ለማጥፋት እየተከናወኑ ያሉት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የጤና ሚኒስትሯ ገለጹ
ጋምቤላ ሚያዝያ 27 /2014(ኢዜአ)...በጋምቤላ ክልል የጊኒ ዎርም በሽታን ለማጥፋት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ ።
ባለድርሻ አካላት ጊኒ ወርምን ለማጥፋት እየተካሄዱ ላሉት ሥራዎች ውጤታማነት ድጋፍና ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
ጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በክልሉ በሽታውን ለማጥፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ትናንት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ዶክተር ሊያ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ጊኒ ዎርምን ከክልሉ ብሎም ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በመንግሥትና በአጋር አካላት እየተከናወኑ ያሉት ስራዎች አበረታችና ተስፋ ሰጪ ናቸው ።
በተለይም እ.ኤ.አ በ2021 በተከናወኑት ስራዎች የበሽታው የስርጭት መጠን ከቀዳሚው ዓመት መቀነሱን ተናግረዋል።
በማሳያነትም እ.ኤ.አ በ2020 በጊኒ ዎርም የተጠቁ 11 ሰዎች እና 15 እንስሳት ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በተከናወኑት ስራዎች በበሽታው የተጠቃ አንድ ሰውና ሦስት እንስሳት ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል።
የበሽታው የስርጭት መጠን መቀነስ የተቻለው የውሃ አማራጭ ባለባቸው ቦታዎች ያቆሩ የውሃ ኩሬዎችን የመድፈንና የውሃ አማራጭ በሌለባቸው ቦታዎች የሚገኙትን የውሃ ኩሬዎች ደግሞ በማከም መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻልን ጨምሮ በባለድርሻ አካላት የተጀመሩት ሥራዎች ተጠናክረው ከቀጠሉ፤ በሽታው ከክልሉ ብሎም ከኢትዮጵያ የሚጠፋበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል።
በመሆኑም በሽታውን ለማጥፋት በፌዴራልና፣ በክልል መንግሥታት እንዲሁም በአጋር ድርጅቶች የተጀመሩት የትብብርና የቅንጅት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በሽታውን ከክልሉ ብሎም ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት በመስራቱ ተጨባጭ ውጤት መታየቱን ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ በቀጣይም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን በሽታውን ለማጥፋት የጀመራቸውን የቅኝትና የምርምር ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የጤና ሚኒስትሯን ጨምሮ በፌዴራልና በጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና በአጋር አካላት ትናንት የተጀመረው የመስክ ምልከታ ዛሬም ቀጥሏል ሲል ኢዜአ ከቦታው ዘግቧል።