ከጦርነት ስጋት ነጻ ሆነን ሰላማዊ ህይወት ጀምረናል- የኤርትራ ስደተኞች - ኢዜአ አማርኛ
ከጦርነት ስጋት ነጻ ሆነን ሰላማዊ ህይወት ጀምረናል- የኤርትራ ስደተኞች
ጎንደር፤ ሚያዝያ 27/2014 (ኢዜአ)ከጦርነት ስጋት ነጻ ሆነው አዲስና ሰላማዊ ህይወት መኖር መጀመራቸውን በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት አለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል የገቡ የኤርትራ ስደተኞች ተናገሩ፡፡
አዲሱ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል በአሁኑ ወቅት ከስምንት ሺህ በላይ የኤርትራ ስደተኞችን እያስተናገደ ሲሆን፣23ሺህ ድረስ ስደተኞችን ለመቀበልመታቀዱን የማዕከሉ ተወካይ ገልጸዋል።
ወጣት ራህስ ነጋሲ ለኢዜአ እንደተናገረው፤ አሸባሪው ህወሃት በአካባቢው ጀምሮ በነበረው ጦርነት ከ''አዲሃሩሽ'' የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በመሸሽ በአሁኑ ወቅት ዳባት በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ይገኛል።
''ትግራይ ውስጥ በነበርንበት ወቅት ቡድኑ በከፈተው ጦርነት በርካታ ስደተኞች ጉዳት ደርሶባቸዋል''ሲል አስታውሷል።
ወደ አዲሱ መጠለያ ማዕከል ከመጣ ጀምሮ ሰላማዊ ህይወት መጀመሩን ገልጿል፡፡
አቶ ኢዮብ ገብረመድህን በበኩላቸው ''ሽመልባ'' በሚባለው የስደተኞች መጠለያ አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ለስምንት ወራት ያህል በጫካ ውስጥ ተደብቀው በአስቸጋሪ ሁኔታ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
''የኢትዮጵያ መንግስት በአፋር በኩል እንድንወጣ ካደረገ በኋላ በአሁኑ ወቅት ዳባት ከተማ በሚገኘው 'የአለም ዋጭ' የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ገብቼ ከጦርነት ስጋት ነጻ የሆነ ህይወት እየመራሁ ነው'' ብለዋል፡፡
''በማዕከሉ ምግብ፣ አልባሳትና መጠለያ አገልግሎት እያገኘሁ ነው፤ ለማዕከሉ የመጠጥ ውሃና የጤና አገልግሎት ሊሟሉለት ይገባል'' ብለዋል፡፡
''በትግራይ ክልል ህንጻጽ በሚባለው የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ የህወሃት ታጣቂዎች በከፈቱት ጦርነት ዘጠኝ ያህል ስደተኞች ህይወታቸው አልፏል'' ያሉት ደግሞ ሌላው ስደተኛ አቶ ሰናይ ትርፌ ናቸው፡፡
በጦርነቱ ምክንያት በርካታ መከራ ማሳለፋቸውን አስታውሰው፤ ''በእግራችን በርሃ አቋርጠን ወደ ዳባት የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ከመጣን ቀን አንስቶ ሰላማዊ ሕይወት ጀምረናል'' ሲሉ ገልጸዋል።
በማዕከሉ አካባቢ ከሚኖረው ማህብረሰብ ጋር ተግባብተውና ተላምደው እየኖሩ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሰናይ፤ በማዕከሉ የመብራት፣ የማገዶ እንጨትና የወፍጮ አገልግሎት እንዲሟሉ ጠይቀዋል፡፡
በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የአለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ተወካይ አቶ ታምራት ደምሴ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ከ8ሺህ በላይ የኤርትራ ስደተኞችን ተቀብሎ እያስተናገደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ ለስደተኞቹ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመጠለያና ሌሎች ሰብአዊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ ወራትም የሚቀበላቸውን ስደተኞች ቁጥር ወደ 23 ሺህ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ በስደተኞቹ የቀረቡትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡