"የአርበኞች ቀን" ሃገራችን ያለችበት አሁናዊ ሁኔታ ተከትሎ፤ ለትውልዱ የሚቸረው ታሪካዊ ትርጉም በእጅጉ የተለየ ያደርገዋል

ሚያዚያ27/2014/ኢዜአ/ ዘንድሮ ለ81ኛ ጊዜ በኩራት የምንዘክረው "የአርበኞች ቀን" ሃገራችን ያለችበት አሁናዊ ሁኔታ ተከትሎ፤ ለትውልዱ የሚቸረው ታሪካዊ ትርጉም በእጅጉ የተለየ ያደርገዋል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን 81ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ለመላው የሃገራችን ህዝብ! ለ81ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ አብሮ አደረሰን።

የአርበኞች ቀንን በልዩ ትኩረት እና ክብደት የምንዘክረው ጀግኖች አርበኞች ለሃገር አንድነት እና ሉዐላዊነት መከበር የከፈሉትን ዋጋ በትውልዱ ዘንድ ተምሳሌታዊ የድል አድራጊነት መንፈስ እንዲጋባ በማሰብ ነው።

May be an image of 14 people, people standing and outdoors

ታሪክ በከፍታ እንደሚገልፀው ጀግኖች አርበኞች በእናት ሃገር ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን በመመከት እና በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ አኩሪ ድሎችን ተቀዳጅተው ነፃና ሉዐላዊት ሃገር አስረክበዋል።

በተለይ ጀግኖች አርበኞች ሀገራችንን ከወራሪ ጠላት ለመጠበቅ በዱር በገደል በመዋደቅ እና አኩሪ ገድል በመፈፀም በትውልድ ቅብብሎሽ የድል አድራጊነት ዘላቂ ፈለግ አውርሰው አልፈዋል።

በዚህ ረገድ ዘንድሮ ለ81ኛ ጊዜ በኩራት የምንዘክረው "የአርበኞች ቀን" ሃገራችን ያለችበት አሁናዊ ሁኔታ ተከትሎ፤ ለትውልዱ የሚቸረው ታሪካዊ ትርጉም በእጅጉ የተለየ ያደርገዋል።

በአሁን ጊዜ በመላው ሃገሪቱ ሰላም እና ፀጥታን በዘላቂነት ከማስፈን አኳያ ለጀመርነው ትግል የቀደሙ ጀግኖቻችንን የድል አድራጊነት ፅኑ መንፈስ ለትውልዱ በማውረስ ረገድ ታሪካዊ ፋይዳው እጅግ የላቀ ነው።

እንዲሁም በዜጎቻችን ላይ የተጋረጡ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን የሚያቀሉ የልማት ውጥኖቻችን በፍጥነት ለማረጋገጥ ከጀመርነው ሁሉአቀፍ ርብርብ አኳያ፤ "የአርበኞች ቀን" የሚያላብሰን ተምሳሌታዊ ትጋት እና ወኔ በልዩነት እና በከፍታ የሚታይ ነው።

እንደሃገር የገጠሙንን ፈተናዎች በፅናት በመሻገር ለመጪው ትውልድ ነፃ፣ ሰላማዊ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማውረስ ዳር እስከዳር አንድነታችንን ማጥበቅ እና መጠበቅ ይገባናል።

በዚህ አጋጣሚ የቀደሙ ጀግኖቻችንን የድል አድራጊነት ታሪክ፤ ዘመኑ በሚጠይቀን የትግል አውድ ላይ ለመድገም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ፅናት በጋራ እንድንቆም አደራ ለማለት እወዳለሁ። መልካም የድል በዓል!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም