ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላችንን ሚና ለመወጣት ዝግጁ ነን-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላችንን ሚና ለመወጣት ዝግጁ ነን-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት
ሚያዝያ 26 /2014(ኢዜአ) ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላችንን ሚና ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የአገራዊ ምክክሩ ምንነትና የአገራት ተሞክሮ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
የምክር ቤቱ ሰብሳቢና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሉጌታ አበበ እንዳሉት፤ የመድረኩ ዓላማ ፓርቲዎች በአገራዊ ምክክሩ ላይ የጠራ ግንዛቤ ይዘው የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ነው።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሰከነ መንገድ ከመወያየትና ከመነጋገር ውጭ የተሻለ አማራጭ አይኖርም ሲሉም ገልጸው ፓርቲያቸው ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኤፍሬም አሰፋ በበኩላቸው፤ በታሪክ አጋጣሚ ሲንከባለሉ የመጡ አለመግባባቶች በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስፈን እንቅፋት እየፈጠሩ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም አለመግባባቶች በውይይት ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን አገራዊ ምክክሩ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ጠቁመዋል።
ብልጽግና ፓርቲ አገራዊ ምክክሩ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ለስኬታማነቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
አገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ለሚስተዋሉት ዘርፈ-ብዙ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ተወካይ ራጎ ሁሉቃ ናቸው፡፡
አክለውም ፓርቲው በምክክር መድረኩ የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ለስኬታማነቱ እንደሚሰራ ተናግረዋል።