ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሴራሊዮን አቻውን በሐዋሳ ይገጥማል

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  ለ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታውን ከነገ በስቲያ በሐዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከሴራሊዮን አቻው ጋር ያደርጋል። በአውሮፓዊያን አቆጣጠር በመጪው ዓመት የሚካሄደውን 32ኛ የአፍሪካ ዋንጫ የምታስተናግደው ካሜሮን ናት። ለዓመቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ። በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 34 ተጫዋቾችን በመያዝ ከነሐሴ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሃዋሳ ልምምድ ሲያደርግ ቆይቷል። በያዝነው ሳምንት ኢንስትራክተር አብርሃም 34 የነበረውን የቡድናቸው ስብስብ ወደ 23 በመቀነስ ከሴራሊዮን ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ እየተጠባበቁ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በማጣሪያው ጨዋታ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ፤ በአንጻሩ ተጋጣሚው ሴራሊዮን ደግሞ ሁለተኛ ድሏን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ጨዋታ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ተጠባቂ ነው። አሰልጣኙ የፊታችን እሁድ የሚያደርጉት ጨዋታ ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ የመጀመሪያቸው የነጥብ  ጨዋታ ይሆናል። ቡድኑ ከሴራሊዮን ጋር ላለበት ጨዋታ ከአምስት ቀናት በፊት ከቡሩንዲ አቻው ጋር በሃዋሳ ስታዲየም ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ አንድ አቻ መውጣቱ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በምድብ አምስት ከኬንያ፣ ጋናና ሴራሊዮን ጋር ተመድቧል። ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያካሄዱት ሰኔ 2009 ዓ.ም ከጋና አቻቸው ጋር በባባ ያራ ስታዲየም  ሲሆን በውጤቱም 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት ተሸንፈዋል። ጋናና ሴራሊዮን የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን በማሸነፍ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን ኬንያ ሶስተኛ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛለች። በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም በፊፋ የአገራት ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃውን ሳይቀይር በነበረበት 151ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በእንግሊዛዊው ጆን ኬይስተር የሚሰለጥነው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ላለበት ጨዋታ 23 ተጫዋቾችን ይዞ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ጨዋታው በሚደረግበት ወደ ሐዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በማምራት ልምምዱን በማድረግ ላይ ይገኛል። ዛሬም ብሔራዊ ቡድኑ ሶስተኛ ልምምዱን ማድረጉን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ከኬንያ ጋር አድርጎ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በድል መጀመሩ የሚታወስ ነው። ለእንግሊዙ ኮቨንትሪ ሲቲ የሚጫወተው አጥቂ አማዱ ባካዮኮ እና የኢንዶኔዥያው ፒኤስአይኤስ የአማካይ ተጫዋች ኢብራሂም ኮንቴህ  ባጋጠማቸው ጉዳት ከቡድኑ ውጭ ሆነዋል። በስዊዘርላንዱ ኤፍሲ ዙሪክ ክለብ የሚጫወተው የቡድኑ አምበል ኡማሩ ባንጉራ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት በእሁዱ ጨዋታ ላይ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን በፊፋ ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ 111ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጥዋል። የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ቱኒዚያዊው ሳዶክ ሰሌሚ ጨዋታውን በረዳት ዳኝነት የሚመሩት የሊቢያና ሩዋንዳ ዳኞች እንዲሁም የሱዳኑ የጨዋታው ኮሚሽነር ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ነገ በሞይ ዓለም አቀፍ የስፖርት ማዕከል ስታዲየም ኬንያ ጋናን ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ታስተናግዳለች። ዋልያዎቹ ሶስተኛ የማጣሪያ ጨዋታቸውን መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከኬንያ ጋር ያደርጋሉ። በካሜሮን በሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 24 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም