ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሻሻል በትኩረት ይሰራል

ሚያዝያ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ)በአሜሪካ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ስለሺ በቀለ የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዲሻሻል በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

አምባሳደሩ ይህን ያሉት ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች እና ሰራተኞች ጋር ትውውቅ ባደረጉበት ወቅት ነው።

በዕለቱ አምባሳደር ስለሺ እንደገለጹት የሚሲዮኑ ባልደረቦች ዋና ትኩረት ዘመናትን ያስቆጠረው የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲሻሻል ሁሉን አቀፍ ጥረት ማድረግ ላይ ይሆናል።

በዳያስፖራ ተሳትፎ፣ ህዝብ ለህዝብ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ ገጽታ ግንባታ፣ ቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች ያለውን ትብብር ማጎልበት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የሚሲዮኑ ባልደረቦች በበኩላቸው የአገራቱ ግንኙነት ዘመናትን ያስቆጠረውን ዲፕሎማሲያዊ መስተጋብር የሚመጥን እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ በሙሉ አቅም እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም