በከተማ ቤቶች ልማት ፕሮግራም 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ነው

188

ሚያዚያ 25/2014(ኢዜአ) በከተማ ቤቶች ልማት ፕሮግራም 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በገጠር የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱ ተገልጿል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በአገሪቱ ከቤት ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ጋር ተያይዞ ያለውን ክፍተት ለመሙላት በሪል ስቴት ልማት ላይ ከተሰማሩ ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የመኖሪያ ቤት እጥረት አገሪቱንና ዜጎችን በእጅጉ እየፈተነና ለከፍተኛ ማኅበራዊ ችግር እያጋለጠ የሚገኝ መሆኑ ይስተዋላል።

እንደ አገር ይህንን የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግር ለመፍታትና ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት በመኖሪያ ቤቶች ልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ገልጸዋል።

በዚህ ሰፊ ኢንቨስትመንትም ባለድርሻ አካላትና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ፣ ፖሊሲዎችን በመከለስና ሰፊ ዕቅዶችን በማቀድ ለዜጎች በአጭርና በረጅም ጊዜ አማራጭ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።  

በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ወስጥ በቤት ልማት ሥራ ዕቅዶች በከተማ ቤት ልማት መርሃ ግብር 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በገጠር የቤት ልማት ፕሮግራም ደግሞ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በከተሞች ለመገንባት ከተያዘው 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤቶች የግል ሴክተሩ 80 በመቶውን እንደሚሸፍን በዕቅድ የተያዘ መሆኑንም ገልጸዋል።  

በሌላ በኩል የከተማ ቤት አቅርቦት የስትራቴጂ ማዕቀፍና የገጠር ቤት ልማት ስትራቴጂ የተሻለ አቅም በሚፈጥርና የግል ሴክተሩን ተሳትፎ በሚያጎለብት መልኩ "የቤት ልማት ስትራቴጂ" በሚል በአንድ ሰነድ ተጠቃሎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።  

ይህም በኢትዮጵያ ከተሞች ተደራሽና ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤቶችን በፍጥነት፣ በጥራትና በብዛት ለማቅረብ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማጎልበት እና ያረጁ የከተማ አካባቢዎችን ለማደስ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ መሆኑንም አክለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የመኖሪያ ቤቶችን እጥረት ለመቅረፍ የተያዘውን እቅድ እንደሚደግፉና ለእቅዱ መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በተለይም በገጠር የሚደረገው የቤቶች ግንባታ ለከተሞች እድገት ባሻገር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን በመቀነስ ረገድም ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ የሚበረታታ ተግባር ነው ብለዋል።

ይሁንና በመኖሪያ ቤቶች ልማት ላይ ያሉ የመሬት አቅርቦትና የፋይናንስ ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።   

የሪል ስቴት ዘርፉ ተገቢው የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅለት፣ ያለውን የቤት ፍላጎት አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማስተናገድ እንዲቻልና የሪል ስቴት አልሚዎችም በተገቢው መንገድ እንዲደራጁ በማስቻል ረገድ የግል ዘርፉ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።

እንዲሁም አልሚዎች ከመንግሥት የሚደረግላቸውን ድጋፍ መጠቀም ላይ ዘርፉን በህግ አግባብ መምራትና በሚያስችሉ ሁኔታዎችም እንዲሁ ተሳትፏቸው የጎላ መሆን እንደሚገባውም ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም