የኦሮሚያ ክልል በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸውን ባለሀብቶች በቅርበት ለመደገፍ ዝግጁ ነው

193

ሚያዝያ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸውን ባለሀብቶች በቅርበት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

የኦሮሚያ ክልል በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

የንቅናቄ መድረኩ አላማ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተገኘውን ውጤት እና በቀጣይ ምን አይነት ስራዎች መሰራት አለባቸው የሚለውን ማሳየት መሆኑ ተገልጿል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ንቅናቄውን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት "የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሳያድግ የሚረጋገጥ ብልጽግና የለም"።

ኢንዱስትሪን ማሳደግ ካልተቻለ ከአለም ጋር መወዳደር እንደማይቻል ገልጸው፤ ባለፉት አመታት ባለሀብቶች በራሳቸው ጥረት በርካታ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት እንደቻሉም ተናግረዋል።

ከነዚህም ኢትዮጵያ እየተጠቀመች እንደሆነ ገልጸው በይበልጥ ለማጠናከር እንዲሁም የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለማድረስ ጠንክሮ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

''ክልሉ ዘርፉን ለማበረታታት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል'' ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በአምራች ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም ገልጸዋል።

መንግስት ዘርፉን ለመደገፍ የቻለውን እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሽመልስ በቀጣይ ከፖሊሲ ማሻሻያዎች ጀምሮ ዘርፉን የሚያበረታቱ ስራዎች እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

ባለሀብቶች ሌብነትን የሚጠየፉ መሆን እንዳለባቸውና ጉዳያቸውን ለማስፈጸም 'እጅ መንሻ' የሚሰጡ መሆን እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው የአምራች ዘርፉ ድህነትን በመቀነስ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

ዘርፉ ውጫዊ እና ውስጣዊ የኢኮኖሚ ተጽእኖዎችን መቋቋም የሚችል እና አስፈላጊ የሆኑ የአሰራር ስርአቶች ከተዘረጉለት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን ማየታቸውን ገልጸዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩ ክፍተቶች መሻሻሎች እንደታየባቸው ገልጸው፤ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የኢንዱስትሪ ሚንስትሩ አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ በክልሉ በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም