ለዘመናት የቆየውን ተቻችሎና ተከባብሮ አብሮ የመኖር እሴትን ለማጠልሸት የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞችን የጋምቤላ ክልል በጽኑ ያወግዛል

110

ሚያዚያ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል መንግስት በአገሪቷ ለዘመናት የቆየውን ተቻችሎና ተከባብሮ አብሮ የመኖር እሴትን ለማጠልሸት የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞችን በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታወቀ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማ ልማትና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቴንኩዌይ ጆክ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም ተጠናቋል።

በክልሉ በዓሉም በሠላም እንዲጠናቀቅ ህዝበ ሙስሊሙና ሌላው የክልሉ ማህበረሰብ ላሳየው ትብብር የክልሉ መንግሥት ልባዊ ምሥጋናውን ያቀርባል ብለዋል።

በዓሉን በሰላም የማክበር ሁኔታ ወደፊትም በሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች በመተባበርና በመደጋገፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በአገሪቱ በሃይማኖቶች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚደረገውን ሙከራ ያወገዙት አቶ ቴንኩዌይ ጆክ፤ በአገሪቷ ለዘመናት የዘለቀውን ተቻችሎና ተከባብሮ አብሮ የመኖር እሴት ለማጠልሸት የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞችን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

ድርጊቱን የክልሉ መንግስት በጽኑ እንደሚያወግዘውም ገልጸዋል።

ጽንፈኞቹ እየሞከሩ ያለውን ሀገር የማፍረስ አጀንዳ የክልሉ መንግስትና ህዝብ አጥብቆ እንደሚቃውም ተናግረዋል።

ጽንፈኛ ቡድኖች የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን ሴራ ለማስፈጸም የሚሰሩ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተገንዝቦ እኩይ ተግባራቸውን ለማከሸፍ ሁሉም በአንድነት ሊቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም