ቀጥታ፡

የጠላቶቻችንን ሴራ እያከሸፍን ብልጽግናችንን እውን እናደርጋለን! ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

አገራችን ለዘመናት በገነባቸው የሕዝቦች አብሮነት ታሪክ በውስጥና በውጪ ጠላቶች በሚሸረብ ሴራ ሳትንበረከክ በብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ ወንድማማችነትን ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገረች ትገኛለች።

በዚህ በሰላማዊ መንገድ ተቻችሎ በሚኖር ሕዝብ መካከል የተለያዩ ሴራዎች ቢቀነባበሩም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን የሚያላሉና ነጻነቱን ለመግፈፍ ለሚታትሩ ጠላቶች እጁን ሳይሰጥ በመደማመጥ ባህሉን፣ ታሪኩንና ቋንቋውን እያሳደገ ይገኛል።

በሕዝብ ትግል ከስልጣን የተወገዱ ሀይሎች ተመልሰው በህዝብ ጫንቃ ላይ ለመውጣት የማያቋርጡት ሸለቆ የማይወጡት ተራራ የለም።

በተመሳሳይ ጽንፈኛ ሀይሎች ሀይማኖትንና ብሔርን ሽፋን በማድረግ በሰላም አብሮ የሚኖር ሕዝብ መሓል መርዝ በመርጨት የጠላቶቻችንን አላማ ለማሳካት ሲታትሩ ይታያል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሕብረ ብሔራዊነትን ለማጎልበትና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ''በፍቅር ተደምረን በአንድነት እንሻገር'' በማለት ቃል ገብቶ መንቀሳቀሱ የጥፋት ሀይሎች በህግ አይጠየቁም ማለት እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል።

ብሔርንና ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚንቀሳቁ ጽንፈኛ ሀይሎች በዛሬው እለት የኢድ አልፈጥር በዓልን ለማክበር በወጣው ሕዝበ ሙስሊም ውስጥ ተደብቀው የውጪ ሀይሎችን ተልዕኮ ለማስፈጸም በአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት ሙከራ በእስልምና እምነት ተከታዮችና በጸጥታ ሀይሎች የተቀናጀ ጥረት ከሽፏል።

አሁንም ሕዝባችን አንድነቱንና አብሮ የመኖር እሴቱን በማጠናከር ሀይማኖትንና ብሔርን ሽፋን አድርገው አገራችንን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎችን ማውገዝ አለበት።

መንግስት የጠላትን ተልዕኮ ያነገቡ ጽንፈኞችና ሽብርተኞች ላይ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚወሰዱ እርምጃዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እየገለጽን የክልላችን ሕዝብና የአገራችን ሕዝቦች ከመንግስት ጎን እንዲቆሙና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ እያስተላለፍን ሕዝበ ሙስሊሙ በጥቂት ሀይሎች በተጠነሰሰው ሴራ ሳይረበሽ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ በዓሉን እንዲያከብር የኦሮሚያ ክልል መንግስት መልዕክቱን ያስተላልፋል።

መልካም በዓል

ሚያዚያ 24 ቀን 2014

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም