በሃይማኖትን ሽፋን ህዝቦችን ለማጋጨት የሚሞክሩ አጥፊዎችን ነቅቶ በመጠበቅ መከላከል ይገባል - የሃይማኖት አባቶች

ሐረር ፤ ሚያዚያ 24 ቀን 2014(ኢዜአ) ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በህዝቦች መካከል ልዩነትን በመፍጠር ለማጋጨት የሚሞክሩ አጥፊዎችን ነቅቶ በመጠበቅ መከላከል እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

1443ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል  በሐረሪ ክልል  ኢማም አህመድ ስታዲየም   ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪን  ጨምሮ ከክልሉና አጎራባች ከተሞች የተውጣጡ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተሳተፉበት ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት በድምቀት ተከብሯል።

ከሃይማኖት አባቶች መካከል የሐረር ታላቁ ጁመዓ መስኪድ ኢማም ሼህ ሙክታር ሀጂ መባረክ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓሉን  የእልምና አስተምህሮት በሚያዘው መሰረት  ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን አቅመ ደካሞችን  በመደገፍ ማሳለፍ አለበት ብለዋል።

የመደጋገፍና አብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በህዝቦች መካከል ልዩነትን በመፍጠር ለማጋጨት የሚሞክሩ አጥፊዎችን ህዝቡ ነቅቶ በመጠበቅ መከላከልና  የተሳሳቱን  መመለስ እንዳለበት  አመልክተዋል።

ወጣቱ ከስሜታዊነት በመቆጠብ ከመንግስትና ከህዝቡ ጋር የጀመረውን የሰላም እና ልማት ስራ ማጠናከር እንደለበትም ተናግረዋል።

ሃጂ መሐመድ ዩስፍ  በበኩላቸው፤ በረመዳን ወር የጀመርነውን በጎ ተግባር እስከመጨረሻው ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል።

በተለይ ያለው የሌለውን በመደገፍ አንድነታችንን ማሳየት አለብን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ሃይሎች እኛን ፈጽሞ አይወክሉም ያሉት ደግሞ አባ ገዳ አህመድ ዩስፍ ናቸው።

ሙስሊምና ክርስቲያን አንድ ናቸው ዛሬም ነገም ወንድማማችነታችንና አብሮነታችንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

አቶ መሐመድ ሰዒድ በሰጡት አስተያየት፤ በተለይ በጎዳና ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን በመመገብና በማልበስ በዓሉን ማክበር ይገባናል ብለዋል።

እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት የተፈናቀሉ ወገኖችንም አይዞህ ልንላቸውና ከጎናቸው ቆመን ልንከባከባቸው ይገባልም ሲሉ አክለዋል።

በሥነ-ሥርዓትላይ  የሐረር ታላቁ ጁመዓ መስኪድ ኢማም ሼህ ሙክታር ሀጂ ሙባረክ ምዕመናኑን ያሰገዱ ሲሆን፤ ህዝበ ሙስሊሙም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ፈጣሪውን እያመሰገነ ወደየመጣበት በሰላም መመለሱን ኢዜአ ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም