ኮሚሽኑ ለዋግ ህምራ ተፈናቃዮች 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ

67

ሰቆጣ ሚያዚያ 23/2014 (ኢዜአ ) የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋትና ልማት ተነሽዎች ኮሚሽን በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።

ከኮሚሽኑ የተላከውን ድጋፍ የብሄረሰብ አስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት ተረክቧል።

ድጋፉን የተረከቡት የብሄረሰብ አስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ ወይዘሮ ዝናሽ ወርቁ ለኢዜአ እንደገለፁት ድጋፉ በሽብር ቡድኑ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማገዝ የተደረገ ነው።
"ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከባለሃብቶችና ማህበረሰቡ ሃብት በማሰባሰብ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማቅረብ ችግራቸውን የመጋራት ስራ እየተከናወነ ነው" ብለዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋትና ልማት ተነሽዎች ኮሚሽን 1ሺህ 300 ኩንታል የዳቦ ዱቄት መላኩን ጠቅሰው፤ ድጋፉ የእርስ በእርስ መተጋገዝን በተግባር ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል።

ድጋፉ በሽብር ቡድኑ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን የምግብ አቅርቦት ችግር የሚያቃልል መሆኑን ተናግረዋል።
ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ቡድን መሪዋ፤ በቀጣይም ሌሎች አካላትና ድርጅቶች የተፈናቃይ ወገኖችን ችግር ለማቃለል መሰል ድጋፎችን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ  ከ86 ሽህ በላይ ወገኖች መኖራቸውን ቡድን መሪዋ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም