የሰለጠነ የመከላከያ የሠው ኃይልን ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰለጠነ የመከላከያ የሠው ኃይልን ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየተሰራ ነው
ሚያዝያ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመከላከያን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የመከላከያ ኅብረት ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል ይመር መኮንን ተናገሩ
የሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መርኃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን የሠራዊት አባላትና ሲቪሎችን አስመርቋል።
የኮሌጁ አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል አበበ ዋቅሹማ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የመከላከያ ሰራዊት የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት እየተሰራ ነው።
የመከላከያ ሚኒስቴር የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሠራዊቱን አቅም የሚያሳድጉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ ለሠራዊቱ የተሰጠውንና ለወደፊት የሚሰጠውን አገራዊ ግዳጅ በአስተማማኝ ብቃትና ጀግንነት ለመፈጸም ተቋማዊ ለውጥ በመገንባት ራሱን ለላቀ ተልዕኮ እያበቃ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመከላከያ ኅብረት ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል ይመር መኮንን በበኩላቸው የመከላከያን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ማዕከል ባደረገ መልኩ ብቃት ያላቸው የቴክኒክ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዕለቱ የተመረቁት የመከላከያ ሰራዊት አባላት በቆይታቸው በቂ ክህሎትና አቅም መጨበጣቸውን ገልጸው በሚመደቡበት የሠራዊት ክፍሎችም ውጤታማ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ተመራቂዎቹ በቆይታቸው የተለያዩ የቴክኒክና የሙያ ሥልጠናዎችን በንድፈ ኃሳብና በተግባር መከታተላቸውን ተናግረዋል።