ቀጥታ፡

በዘንድሮው የረመዳን የጾም ወቅት የታየው መረዳዳትና መተጋገዝ በኢድ አል-ፈጥር በዓል መድገም ይገባል

ሚያዝያ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዘንድሮው የረመዳን የጾም ወቅት በተለያዩ የዓለም አገራት ያሉ የእምነቱ ተከታዮች ወደ አገራቸው የከተሙበት እንዲሁም የህዝቡ አንድነት ጎልቶ የታየበት መሆኑ ለየት ያደርገዋል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ተናገሩ።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ በአገር ውስጥና በተለያዩ የዓለም አገራት ላሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህም ሕዝበ ሙስሊሙ የዘንድሮው የረመዳን የጾም ወቅት በመተሳሰብ፣ በመረዳዳትና በመደጋገፍ ማሳለፍ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በተለይም ከ"ኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት ጉዞ'' ጥሪን ተቀብለው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መምጣታቸው ደግሞ ልዩ ድምቀት መፍጠሩን ተናግረዋል።

ወደ አገራቸው እየገቡ ላሉ እንግዶች ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነው፤ ለእንግዶቹ የሚደረገው እንክብካቤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የረመዳን የጾም ወቅት በሰላም እንዲከናወን ላበረከተው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።

በመዲናዋ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተደረገው የኢፍጣር መርሃ-ግብር እጅግ ደማቅ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም የዜጎችን አብሮነት በተግባር ማሳየቱን አብራርተዋል።

በከተማ ደረጃ የተካሄደው የኢፍጣር መርሃ-ግብር ሰላማዊ በሆነና በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ከፍተኛ ሚና ለተወጡት የጸጥታ አካላት ምስጋና አቅርበው፤ ሕዝበ ሙስሊሙ ያሳየውን ጨዋነት አድንቀዋል።

በጾሙ ወቅት በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለማገዝ የተደረገው ትብብር በበዓሉ ወቅት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም